በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን የሰላም እና ፍትህ ቢሮ የተዘጋጀ የልምድ ልውውጥ መድረክ ተካሄደ በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን የሰላም እና ፍትህ ቢሮ የተዘጋጀ የልምድ ልውውጥ መድረክ ተካሄደ 

በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን የሰላም እና ፍትህ ቢሮ የተዘጋጀ የልምድ ልውውጥ መድረክ ተካሄደ

የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ማህበራዊ እና ልማት ኮሚሽን ሥር በሚተዳደረው የሰላም እና ፍትህ ቢሮ የተዘጋጀ የልምድ ልውውጥ መድረክ ሞጆ በሚገኘው የኮንሶላታ ልዑካን የሱባኤ ማዕከል ከሚያዚያ 3 እስከ 4 ቀን 2017 ዓ.ም. ድረስ የተካሄደ ሲሆን፣ በዚህ የልምድ ልውውጥ መድረክ ከተለያዩ ጉባኤዎች የመጡ ገዳማዊያት፣ አረጋዊያን አባቶች፣ ከየቁምስናው የተወከሉ ሰላም ግንባታ ላይ የሚሰሩ ባለሙያዎች እና ወጣቶች ተሳትፈዋል።

አዘጋጅ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ  

መርሃ ግብሩን በቡራኬ እና በመግቢያ ሃሳብ ያስጀመሩት የኮንሶላታ ማህበር ካህን አባ ዳዊት ዳንኤል የዚህ ዓይነት የልምድ ልውውጥ መድረኮች ለሰላም ግንባታ ሂደት ያላቸውን ጠቀሜታ እና የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሰላምን ለማበረታታት ዘርፈ ብዙ ሥራዎችን በሃገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች እየሰራች እንደምትገኝ በመጥቀስ፥ ሁሉም ተሳታፊ ከመድረኩ ያገኘውን ዕውቀት እና ልምድ በየተሰማራበት የሥራ ዘርፍ ላይ ተግባራዊ እንዲያደርገው አደራ ብለዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ በዐቢይ ፆም መግቢያ ላይ ለምዕመናን ባስተላለፉት ሃዋሪያዊ መልዕክት “በጋራ የመጓዝን” አስፈላጊነትን ማሳሰባቸው የሚታወስ ሲሆን፥ ይህ መድረክ ሁሉንም የዕድሜ ክልል ያማከለ በመሆኑ እና በማሳተፉ አብሮ የመጓዝ መንፈሳችንን ያጠናክራል ተብሏል።

ዝግጅቱ በዋናነት ዓላማ አድርጎ ካነጣጠረባቸው ግቦች መካከል በአረጋውያን እና በወጣቱ ትውልድ መካከል ያለውን ግንኙነት ለማስማማት፣ የአረጋውያንን የበለጸጉ ተሞክሮዎችን ለወጣት ትውልድ ለማካፈል፣ እንዲሁም ወጣቱ ትውልድ ዘመናዊውን እና ትውፊታዊ አካሄድን በማቀናጀት ቤተ ክርስቲያንን እና ሀገርን የበለጠ በማልማት ለትውልድ እንዲተላለፍ ማድረግ እንዲችል ለመርዳት እንደሆነ ተገልጿል፣  

ከመድረኩ አዘጋጆች ለመረዳት እንደተቻለው ይህ ሁሉንም የእድሜ ክፍል ያካተተው የውይይት መድረክ በተለያየ ዘመን የኖሩ ትውልዶች አብረው ቁጭ ብለው ስለ ሰላም እና ፍትህ የሚመካከሩበት እና ልምድ የሚለዋወጡበት መድረክ መሆኑን የገለጹ ሲሆን፥ በሃገራችን እና ቤተክርስቲያናችን ደረጃ በሰላም እና ፍትህ ዙሪያ ለሚሰሩ ዘርፈ ብዙ ሥራዎች በእንደዚህ ዓይነት የንግግር ጊዜያቶች ከተሳታፊዎች የሚሰበሰቡ ግብአቶች ለሰላም ግንባታው ትግበራ ግብአት ሆነው ስለሚያገለግሉ እና ስለሚጠቅሙ መርሃ ግብሩ እጅግ አስፈላጊ እንደሆነ ተገልጿል።

በልምድ ልውውጥ መድረኩ የመጀመሪያ ቀን ተሳታፊዎች በንኡስ ቡድኖች በመከፋፈል በህይወት ዘመናቸው ያሳለፉትን እና ለሌሎች ትምህርት ይሆናል ብለው ያሰቡትን ልምዶቻቸውን የማካፈል ጊዜን ያሳለፉ ሲሆን፥ ከዚህ በትውልዶች መካከል በተደረገው የውይይት መድረክ መርሃ ግብር መጨረሻ ተሳታፊዎች በርካታ ልምዶችን እና ትምህርት እንደሚጨብጡ ተነግሯል። 

ከእነዚህም መካከል በቤተክርስቲያኒቱ እና እንደ ሀገር የተፈጠረውን የትውልዶች ልዩነት ለማጥበብ ጥልቅ ጠቀሜታ እንዳለው ብሎም የውይይት መድረኩ የታላላቆችን ጥበብ ከዚህ ትውልድ ወጣት የፈጠራ ክህሎት እና አቅም ጋር የማሰናሰል እድል እንደሚፈጥር፣ የጋራ የሆነ መከባበርን እንደሚገነባ፣ የህይወት ቀጣይነትን ከለውጦች ጋር አዋህዶ ለማስቀጠል፣ ከመወቃቀስ የዘለለ የጋራ ሃላፊነትን መቀበልን ለማስቻል እንዲሁም ማህበራዊ ትሥሥርን እና ፈውስን እንደሚያስገኝ ተመላክቷል።

ከዚህም ባሻገር በአገር አቀፍ፣ በሀገረ ስብከት፣ በጉባኤዎች እና በቁምስና ደረጃ ያሉ የልምድ መጋራት ዝግጅቶች እንዲካሄዱ ይህ መርሃግብር እንደ ቅድመ ሁኔታ ሆኖ ስትራቴጂ ለማውጣት እንደሚያገለግልም ተገልጿል።

በዝግጅቱ ወቅት ከተከናወኑት ተግባራት መካከል፥ ለተወሰኑ አረጋውያን ቃለ መጠይቅ ማድረግን ጨምሮ፣ ተሳታፊዎች በተለያዩ ቡድኖች ተካፍለው የመረብኳስ፣ የጠረጴዛ ቴኒስ እና የጆተኒ ጨዋታዎችን ተጫውተዋል፣ ብሎም የተለያዩ የማህበራዊ ምሽት ጊዜያትን አሳልፈዋል።  

 

 

14 Apr 2025, 18:01