ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ለታዳጊ ወጣትቶች የቪዲዮ መልዕክት ባስተላለፉበት ወቅት ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ለታዳጊ ወጣትቶች የቪዲዮ መልዕክት ባስተላለፉበት ወቅት 

ነፍስሔር ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ወጣቶች ሌሎችን ማዳመጥን መማር እንደሚገባ አሳስበው ነበር

የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በጥር ወር አጋማሽ ለሕክምና ሆስፒታል ከመግባታቸው አንድ ወር አስቀድመው ባስተላለፉት የቪዲዮ መልዕክት፥ ወጣቶች ሌሎችን ማዳመጥ አስፈላጊ መሆኑን አሳስበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የማዳመጥን አስፈላጊነት በማስመልከት በታኅሳስ ወር የተዘጋጀው የቅዱስነታቸው የቪዲዮ መልዕክት ስብሰባውን ለሚካፈሉት ወጣቶች ያደረጉትን ንግግር የሚሳይ እንደ ነበር ታውቋል።

ጣሊያን ውስጥ በሉካ ድሩሲያን የተጀመረው ይህ ተነሳሽነት ወጣቶችን እና ጎልማሶችን በማሰባሰብ በተለያዩ ርዕሠ ጉዳዮች ላይም የተወያየ እና እንዲሁም ሌሎችን የማዳመጥ እና የመስማትን ጥቅም ለመገምገም ተስፋ ያደረገ እንደ ሆነ ተመልክቷል።

የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የቪዲዮ መልዕክት “ኦጂ” (ዛሬ) በተሰኘው የጣሊያን ሳምንታዊ መጽሔት ይፋ የሆነው ቅድሜ ሚያዝያ 18/2017 ዓ. ም. ከተፈጸመው የቀብር ሥነ-ሥርዓት በኋላ እሑድ ሚያዝያ 19/2017 ዓ. ም. እንደ ሆነ ታውቋል።  

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቅድስት ማርታ መኖሪያ ቤታቸው ውስጥ ሆነው ባስተላለፉት የቪዲዮ መልዕክት ላይ፥ “ወጣቶች የዘወትር አስተማሪዎቻቸው የሆኑ አያቶቻችሁን ማዳመጥ ይገባል” ሲሉ አሳስበዋል።

የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመልዕክታቸው፥ ልጆች በሕይወታቸው ውስጥ ካሉት እጅግ አስፈላጊ ነገሮች መካከል አንዱ ማዳመጥ እና እንዴትስ ማዳመጥ እንዳለባቸው መማር እንደሆነ አስገንዝበው፥  የአንድን ሰው ንግግር በትክክል ለመረዳት ንግግሩን እስከ መጨረሻው ድረስ ማዳመጥ እና አስፈላጊ ከሆነም መልስ መስጠት እንደሚገባ አሳስበው ዋናው ነገር ግን ማዳመጥ እንደ ሆነ አስረድተዋል።

ነፍስሔር ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቪዲዮ መልዕክታቸው፥ ብዙ ሰዎች ሌላው ሰው በሚናገሩበት ወቅት ምላሻቸውን እያዘጋጁ ስለሆነ በትክክል ማዳመጥ እንደማይችሉ ተናግረዋል።

“ሰዎችን በቅርበት ከተመለከታችኋቸው ሌሎችን በትክክል አያድሳምጡም” ያሉት ቅዱስነታቸው፥ ማብራሪያቸውን ገና ሳይጨርሱ መልስ ለመስጠት እንደሚቸኩሉ እና ይህም በመካከላቸው ሰላምን ለማምጣት የማይረዳ በመሆኑ በቅድሚያ በሚገባ ማዳመጥ እንደሚገባ አሳስበዋል።

የነፍስሔር ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የቪዲዮ መልዕክት ይፋ የሆነው በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ታዳጊዎች የኢዮቤልዩ በዓላቸውን  ለማክበር ሚያዚያ 19/2017 ዓ. ም. በሮም በተሰበሰቡበት ወቅት እንደ ነበር ታውቋል።

ወደ 200,000 የሚጠጉ የበዓሉ ታዳሚዎች እሑድ ዕለት በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ የተገኙት ለቅዱስነታቸው ዘጠኝ የሐዘን ቀናት በታወጀ በሁለተኛው ቀን እንደ ነበር ታውቋል።

ብፁዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን፥ ዕለቱ የመለኮታዊ ምሕረት በዓል የተከበረበት ቢሆንም፥ በአደባባዩ ለተገኙት ታዳጊዎች ባስተላለፉት መልዕክት፥ ልጆች ለእርስ በርስ ግንኙነት እና ለመላው ዓለም የሰላም መንገድን ለማግኘት ሟቹ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ያስተማሩትን ትምህርት ተግባራዊ እንዲያደርጉት አደራ ብለዋል።

 

28 Apr 2025, 17:16