የር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስን የሕይወት ታሪክ የሚያስታውስ ጽሑፍ በአስከሬናቸው ሳጥን ውስጥ ተካተተ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ከርቡዕ ጀምሮ ባሉት ሦስት ቀናት ውስጥ ወደ 250,000 የሚገመቱ ምዕመናን፣ ነጋዲያን እና እንግዶች ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ያላቸውን አክብሮት ከገለጹላቸው በኋላ ዓርብ አመሻሽ ላይ በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ውስጥ የአስከሬናቸው ሳጥን በጸሎት ሥነ-ሥርዓት ታሽጓል።
እንደ ቤተ ክርስቲያኒቱ ባሕል መሠረት በርዕሠ ሊቃነ ጳጳስነት ዓመታትን ያከናወኗቸውን ሐዋርያዊ ተግባራትን የሚያስታውሱ በስማቸው የተቀረጹ ሳንቲሞችን እና ሜዳሊያዎችን ጨምሮ ሙሉ የሕይወት ታሪካቸውን የያዘ ጽሑፍም በአስከሬናቸው ሳጥን ውስጥ መካክተቱን የቅድስት መንበር መግለጫ አስታውቋል። የቅዱስነታቸውን የሕይወት ታሪክ የሚያስታውስ ጽሕፍ እንደሚከተለው ይነበባል፥
ታላቁ ግባችን ወደ ሆነው መንግሥተ ሰማያት የተጠራንን የተስፋ ነጋዲያንን ሲመሩን የነበሩ ተወዳጁ የቤተ ክርስቲያን እረኛ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ በቅዱስ ዓመት የብርሃነ ትንሳኤው ማግስት ሰኞ ሚያዝያ 13/2017 ዓ. ም. ከጠዋቱ አንድ ሰዓት ከሰላሳ አምስት ደቂቃ ከዚህ ዓለም ተለይተው ወደ አብ ዘንድ ሄደዋል። መላው የክርስቲያን ማኅበረሰብ በተለይም ድሆች ደፋር እና ታማኝ የወንጌል አገልጋይ ስለሰጥን እግዚአብሔርን እናመሰግነዋለን። የካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን 266ኛ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት የነበሩት የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ትውስታ በቤተ ክርስቲያን እና በሰው ልጆች ልብ ውስጥ ይኖራል።
በቀድሞው ስማቸው ጆርጅ ማሪዮ ቤርጎሊዮ በመባል የሚታወቁት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በአርጄንቲና መዲና ቦይኔስ አይረስ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በታኅሣሥ 17 ቀን 1936 ዓ. ም. ከስደተኛ ቤተሰብ ተወለዱ። አባታቸው ማሪዮ በባቡር መንገድ ድርጅት ውስጥ የገንዘብ ሹም ነበሩ። እናቱ ሬጂና ሲቮሪ ግን የቤት እመቤትነት ስለነበሩ አምስት ልጆቻቸውን ይንከባከቡ ነበር። ጆርጅ ማሪዮ ቤርጎሊዮ በኬሚስትሪ ቴክኒሻንነት በዲፕሎማ ከተመረቁ በኋላ የክህነት ሕይወትን መረጡ። እንደ ጎርጎሮሳውያኑ መጋቢት 11/1958 ዓ. ም. በሀገረ ስብከታቸው በሚገኝ የዘርዓ ክህነት ትምህርት ቤት ከገቡ በኋላ በኢየሱሳውያን ማኅበር ውስጥ እንደ ጀማሪ ተማሪነት የምንኩስና ሕይወታቸው ቀጠሉ። በቺሊ ውስጥ የማኅበረሰብ ጥናቶችን ከተከታተሉ በኋላ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ 1963 ዓ. ም. ወደ አርጀንቲና ተመልሰው በሳን ሚጌል በሚገኘው ቅዱስ ጁሴፔ ኮሌጅ በፍልስፍና ትምህርት ተመረቁ። በቦነስ አይረስ በሳንታ ፌ በሚገኘው የእመቤታችን ንጽሕት ድንግል ማርያም ኮሌጅ የሥነ-ጽሑፍ እና የሳይኮሎጂ መምህር ነበሩ።
እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በታኅሳስ 13/1969 ዓ. ም. ከሊቀ ጳጳስ ራሞን ሆሴ ካስቴላኖ የክህነት ማዕረግ ተቀበሉ። በሚያዝያ 22/1973 ዓ. ም. በኢየሱሳውያን ማኅበር የመጀመሪያ መሐላቸውን ፈጸሙ። በሳን ሚጌል ውስጥ በቪላ ባሪላሪ የዘርዓ ክህነት የጀማሪዎች አለቃ ሆነው ካገለገሉ በኋላ በሥነ-መለኮት የትምህርት ዘርፍ ውስጥ በመምህርነት ሲሰሩ ቆይተው በአርጄንቲና የኢየሱሳውያን ማኅበር አማካሪ እና የኮሌጁ ሃላፊ ሆነው አገልግለዋል። እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ከ1986 በኋላ በጀርመን የዶክትሬት ትምህርታቸውን አጠናቅቀው ወደ አርጄንቲና ሲመለሱ ካርዲናል አንቶኒዮ ኳራሲኖ የቅርብ ተባባሪያቸው አደረጓቸው።
የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ግንቦት 20/1992 ዓ. ም. የአውካ ጳጳስ እና የቦይነስ አይረስ ረዳት ጳጳስ አድርገው የሰየሟቸው አቡነ ጆርጅ ማርዮ ቤርጎሊዮ “Miserando atque eligendo” ወይም “በአዘኔታ እና በምርጫ” የሚለውን እንደ መሪ ቃል በመምረጥ “HIS” የኢየሱሳውያን ማኅበር ምልክት ለጵጵስናቸው ይሆን ዘንድ መረጡ።
እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ሰኔ 3/1997 ዓ. ም. የቦይነስ አይረስ ተባባሪ ሊቀ ጳጳስ ሆነው የተሰየሙት አቡነ ጆርጅ ማርዮ ቤርጎሊዮ በየካቲት 28/1998 ዓ. ም. ካርዲናል ኩራሲኖ ሲሞቱ በአርጄንቲና ለሚኖሩ የምሥራቅ ቤተ ክርስቲያን ሥርዓት ተከታይ ምዕመናን መጋቢ እና የካቶሊክ ዩኒቨርሲቲ ታላቅ ቻንስለር ሆነው ተሰየሙ።
የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ በየካቲት 21/2001 ዓ. ም. የቅዱስ ሮቤርቶ ቤላሪሚኖን ማዕረግ በመስጠት የካርዲናልነት ማዕረግ ሰጧቸው። በጥቅምት ወር በተካሄደው የጳጳሳት ሲኖዶስ አሥረኛው መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ረዳት ሪፖርት አቅራቢ ሆነው አገልግለዋል። ካርዲናል ጆርጅ ማርዮ ቤርጎሊዮ በሀገረ ስብከታቸው ትሁት እና ተወዳጅ ሐዋርያዊ አባት ነበሩ። ለአገልግሎት ከቦታ ወደ ቦታ በሚጓዙበት ወቅት የሕዝብ ማመላለሻዎችን ይጠቀሙ ነበር። ራሳቸውን በሌሎች ሰዎች መካከል እንደ አንዱ ይመለከቱ ስለ ነበር ምግባቸውን ጭምር ራሳቸው ያዘጋጁ ነበር።
የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቤነዲክቶስ 16ኛ ስልጣን መልቀቃቸውን ተከትሎ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ መጋቢት 13/2013 ዓ. ም. በተሰበሰበው የካርዲናሎች ጉባኤ ላይ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት እንዲሆኑ ተመረጡ። የአሲሲውን ቅዱስ ፍራንችስኮስ ምሳሌ በመከተል በዓለም ዙሪያ የሚገኙ እጅግ ድሃ የሆኑትን ለመንከባከብ ባላቸው ፍላጎት ስማቸውን ፍራንችስኮስ ብለው ለመሰየም ወደዱ። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳስ ሆነው በተመረጡበት ዕለት በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ሰገነት በኩል ቀርበው የሚከተለውን ንግግር አሰምተዋል።
“ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደ ምን አመሻችሁ! ጳጳስ እና ምዕመናን ሆነን አንድ ላይ ይህን ጉዞ በኅብረት መጓዝ እንጀምራለን፤ ይህ የሮም ቤተ ክርስቲያን የጋራ ጉዞ ሁሉንም ቤተ ክርስቲያናት በበጎነት ይመራል። የወንድማማችነት፣ የፍቅር እና የመተማመን ጉዞ ነው” ካሉ በኋላ በማጎንበስ፥ “እግዚአብሔር በአገልግሎቴ እንዲባርከኝ፣ ለጳጳሳችሁ ቡራኬን ከእግዚአብሔር ዘንድ በጸሎታችሁን እንድትጠይቁ እለምናችኋለሁ።” ካሉ በኋላ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ መጋቢት 19/2013 ዓ. ም. በቅዱስ ዮሴፍ ክብረ በዓል ዕለት የቤተ ክርስቲያን ሐዋርያዊ አገልግሎታቸውን በይፋ ጀመሩ።
በማኅበረሰቡ ዘንድ ለተናቁት ዘወትር የሚጨነቁት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለከፍተኛ ሐዋርያዊ አገልግሎት በተመረጡበት ወቅት በቅድስት ማርታ የጳጳሳት መኖሪያ ቤት ውስጥ መኖርን መረጡ። ይህን ያደረጉት ከሰዎች ጋር ሳይገናኙ መቆየት ስለማይፈልጉ እና ከመጀመሪያው ጀምሮ ጸሎተ ሐሙስን ከቫቲካን ውጥተው ታራሚዎችን እና የአካል ጉዳተኛ ማዕከላትን በመጎብኘት እንዲሁም ከአደንዛዥ ዕፅ ሱሰኞች ጋር ለማክበር ስለ ወደዱ ነበር። ካህናት ምዕመናንን ንስሐን ለማስገባት ምን ጊዜም ዝግጁዎች እንዲሆኑ፣ ከቅድስተ ቅድሳት ወጥተው የጠፉትን ለመፈለግ ድፍረት እንዲኖራቸው፣ ከእግዚአብሔር አብ ጋር ለመገናኘት የሚፈልጉትን ለመቀበል የቤተ ክርስቲያኖቻቸውን በሮች እንዲከፈቱ አሳሰቡ።
ለሐዋርያዊ አገልግሎት ያላሰለሰ ጥረት በማድረግ ከሙስሊሞችን ጨምሮ ከሌሎች የሃይማኖት መሪዎች ጋር ለመወያየት፣ አንዳንድ ጊዜ ለጋራ ጸሎት በመጋበዝ በልዩ ልዩ የእምነት ተከታዮች መካከል ግንኝነትን የሚያሳድግ የሰው ልጆች ወንድማማችነት የጋራ ሠነድን እንደ ጎርጎሮሳውያኑ የካቲት 4/2019 ዓ. ም. በአቡ ዳቢ ከተማ ከሱኒ መሪ አል-ጣይብ ጋር ተፈራረሙ። ለድሆች፣ ለአረጋውያን እና ለህጻናት ያላቸው ፍቅር የዓለም የድሆች ቀንን፣ የአያቶች እና የህፃናት ቀንን እንዲያውጁ አድርጓቸዋል። የእግዚአብሔርን ቃል ሰንበትንም አስጀምረዋል።
ከቀደሙት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት በላይ የጠቅላላ ካርዲናሎች ቁጥር በማሳደግ በ 73 አገራት ውስጥ ከእነዚህም ከዚህ በፊት ካርዲናል ባልነበረባቸው 23ቱ አገራት ጭምር መምረጥ የሚችሉ 133 ካርዲናሎችን እና መምረጥ የማይችሉ 30 ካርዲናሎችን ሰየሙ።
አምስት የብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤዎች እንዲካሄዱ ያደረጉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ ከእነዚህ መካከል ሦስቱ መደበኛ የጳጳሳት ጉባኤዎች በቤተሰብ፣ በወጣቶች እና በሲኖዶሳዊነት ላይ የተካሄዱ ሲሆን፥ ቤተሰብን የተመለከተ ልዩ የብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ እና በፓን-አማዞኒያ ክልል የተካሄደው ልዩ የጳጳሳት ሲኖዶስ ይገኝበታል።
ንፁሐንን ከጥቃት ለመከላከል ብዙ ጊዜ ድምጻቸው ሲያሰሙ የነበሩት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በተከሰተ ጊዜ የሰው ልጅ በማይታወቅ የመቅሰፍት ፍርሃት ውስጥ በመውደቁ እና በመሰቃየቱ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ መጋቢት 27/2020 ዓ. ም. ምሽት ላይ በምሳሌያዊ ሁኔታ የሮም ከተማን እና መላው ዓለምን ያቀፈው የጸሎት ሥነ-ሥርዓትን በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ብቻቸውን ፈጽመዋል። በርዕሠ ሊቃነ ጵጵስናቸው የመጨረሻዎቹ ዓመታት በተለያዩ አገሮች በተለይም በዩክሬን፣ በፍልስጤም፣ በእስራኤል፣ በሊባኖስ እና በምያንማር በተካሄዱ ሦስተኛ የዓለም ጦርነት በሚመስሉ ውጊያዎች መካካል የሰላም ጥሪያቸውን አቅርበዋል።
እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ከሐምሌ 4/2021 ዓ. ም. ጀምሮ ጄሜሊ ሆስፒታል ለቀዶ ጥገና ሕክምና ገብተው ለአሥር ቀናት ሕክምና ሲከታተሉ ቆይተው ከተመለሱ በኋላ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ የካቲት 14/20125 ዓ. ም. ለሳንባ ምች ሕመም እንደገና ተመልሰው ሆስፒታል ገብተው ሙሉ በሙሉ ባያገግሙም ራሳቸውን ለሐዋርያዊ አገልግሎት እስከመጨረሻው በመሰጠታቸው የመጨረሻዎቹን ሳምንታት በቅድስት ማርታ መኖሪያቸው አሳልፈዋል። በብርሃነ ትንሳኤው በዓል ዕለት እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ሚያዝያ 20/2025 ዓ. ም. ለመጨረሻ ጊዜ በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ሰገነት በኩል በመታየት ለሮም ከተማ እና ለመላው ዓለም ቡራኬያቸውን ሰጥተዋል።
የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ አስተምህሮዎች እጅግ ጥልቅ ናቸው። በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ከራስ ወዳድነት እና ከመንፈሳዊ ዓለማዊነት ወጥመዶች ለመራቅ የሚያግዙ በወንጌል ተልዕኮ ግልጽነት፣ በሐዋርያዊ ድፍረት እና በምሕረት ላይ የተመሠረተ “Evangelii gaudium” ወይም የወንጌል ደስታ የሚለውን
ሐዋርያዊ ማሳሰቢያቸውን ለሐዋርያዊ መርሃ ግብራቸው መነሻ በማድረግ እንደ ጎርጎሮሳስውያኑ ህዳር 24/2013 ዓ. ም. ይፋ አደረጉ። ከዋና ዋና ሐዋርያዊ ሠነዶቻቸው መካከል የመጀመሪያውን እና በእግዚአብሔር ማመን “Lumen fidei” ወይም “የእምነት ብርሃን” የሚለውን እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በሰኔ 29/2013 ይፋ ያደረጉ ሲሆን፥ “Laudato si” ወይም ውዳሴ ላንተ ይሁን” የሚለውን ሐዋርያዊ ሠነድ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በግንቦት 24/2015 ዓ. ም. ይፋ አደረጉ። የአየር ንብረት ቀውስ፣ የሥነ-ምህዳር እና የሰው ልጅ ሃላፊነት በማስመልከት በሰዎች ወንድማማችነት እና በማኅበራዊ ወዳጅነት ላይ “Fratelli tutti” ወይም “ሁላችንም ወንድማማቾች ነን” የሚለው ሐዋርያዊ ሠነድ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ጥቅምት 3/2020 ዓ. ም. ይፋ አደረጉ። እጅግ በተቀደሰው የኢየሱስ ክርስቶስ ልብ ላይ እና “Dilexit nos” ወይም “እርሱ ወደደን” የሚለው ሐዋርያዊ ሠነድ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ጥቅምት 24/2024 ዓ. ም. ይፋ አደረጉ።
ሰባት ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳኖችን፣ ሠላሳ ዘጠኝ ደንቦችን፣ በርካታ ሐዋርያዊ መልዕክቶችን እና የግል ውሳኔዎችን፣ ሁለት ቅዱስ ዓመቶችን ጨምሮ በርካታ የጠቅላላ ትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮችን እና በዓለም ዙሪያ የሐዋርያዊ ጉብኝት ንግግሮቻቸውን አበርክተዋል። አዲስ የቫቲካን መገናኛ ጽሕፈት ቤትን እና የኢኮኖሚ ጽሕፈት ቤትን ያቋቋሙ ሲሆን፥ የምእመናን፣ የቤተሰብ እና የሕይወት እንዲሁም አጠቃላይ የሰው ልጅ ዕድገትን ለማበረታታት አዲስ ጽሕፈት ቤቶችን ካቋቋሙ በኋላ የቅድስት መንበር ከፍተኛ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤቶችን ለማደስ በወሰዱት እርምጃም “Praedicate Evangelium” ወይም “ወንጌልን ስበኩ” የተሰኘ ሐዋርያዊ ደንብ እንደ እጎርጎሮሳውያኑ መጋቢት 19/2022 ዓ. ም. ይፋ አድርገዋል።
(Mitis et misericors Iesus እና Mitis Iudex Dominus Iesus) በሚል የጋብቻ ጉዳዮችን ውድቅ የሚያደርግ ሕገ ቀኖናዊ ሂደትን ያሻሻሉ ሲሆን፥ ለአካለ መጠን ባልደረሱ ሕጻናት ወይም ራሳቸውን ለመከላከል አቅም በሌላቸው ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን የሚመለከት “Vos etis lux mundi” የተሰኘ ሕግን አጠናክረዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለሰው ልጆች በሙሉ አስደናቂ የቅድስና ሕይወት እና የዓለማቀፋዊ አባትነት ምስክርነት ትተው አልፈዋል።
“ቅዱስ አባታችን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ነፍስዎት በኢየሱስ ክርስቶስ ዘንድ ለዘለዓለም ትረፍ!”