ካርዲናል ባልዳዛር፥ “ቤተ ክርስቲያን በዚህ ወቅት እረኛ እንደሌላት መንጋ ይሰማታል” ሲሉ ገለጹ

በካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ጥንታዊ ትውፊት መሠረት የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳትን ዕረፍት ምክንያት በማድረግ በመስዋዕተ ቅዳሴ የታገዘ ዘጠኝ የሐዘን ቀናት ከተጀመረ እነሆ ሦስተኛ ቀኑን ይዟል። በዚህ መሠረት ሰኞ ሚያዝያ 20/2017 ዓ. ም. በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ የመስዋዕተ ቅዳሴ ሥነ-ሥርዓት ተፈጽሟል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ከቀትር በአሥራ አንድ ሰዓት ላይ የቀረበውን መስዋዕተ ቅዳሴ የመሩት ብፁዕ ካርዲናል ባልዳዛር ሬይና፥ የሮም ሀገረ ስብከት ረዳት ጳጳስ ሲሆኑ፥ በሥነ-ሥርዓቱ ላይ በርካታ ካርዲናሎች፣ ብጹዓን ጳጳሳት፣ ካህናትን እና ደናግል እንዲሁም የሮም ሀገረ ስብከት ምዕመናን ተካፋይ ሆነዋል።

ብፁዕ ካርዲናል ባልዳዛር ሬይና ለነፍስሔር ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በተደረገው ሦስተኛ የሐዘን ቀን መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ ባሰሙት ስብከት፥ “እኛ የሮም ሀገረ ስብከት ምእመናን በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ዕረፍት የተነሳ ከመላው ዓለም ካቶሊካዊ ምዕመናን ጋር ሐዘን ተሰምቶናል” ሲሉ ገልጸው፥ ሐዘን ብቻ ሳይሆን “እረኛ እንደሌለው መንጋ ይሰማናል” ብለዋል። “በእርሻ ላይ የተዘራ እህል ፍሬ እንዲያፈራ መሞት አለበት” ያሉት ካርዲናል ባልዳዛር፥ ሞት የመጨረሻ እንዳልሆነም አስታውሰዋል።


“በተሰበረ ዓለም ውስጥ እረኛ እንደ ሌለው መንጋ”

የሮም ሀገረ ስብከት ረዳት ብፁዕ ካርዲናል ባልዳዛር ሬይና፥ “እረኛ እንደሌላቸው በጎች ይሰማናል” በማለት በጀመሩት ስብከታቸው፥ ይህ አባባል የእነዚህን ቀናት ስሜት ጠቅለል አድርጎ የሚገልጽ እና የሰው ልጅ አሁን የሚገኝበትን ሁኔታ የሚያንፀባርቅ እንደሆነ ተናግረው፥ ይህም ችግር በሞላበት ዓለም ውስጥ ኢየሱስ ክርስቶስ እንዲራራለት የተተወ እና መሪ የሌለውን ሕዝብ የሚያስመስል እንደሆነ አስረድተዋል።

“ሕይወት እና በጎነት ሞትን እና ክፋትን ያሸንፋሉ!”

ብፁዕ ካርዲናል ባልዳዛር ሐዋርያት በአገልግሎታቸው ውስጥ ድካም ቢሰማቸውም ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ ለተሰበረ ዓለም የተስፋ ምልክቶችን እና ተጨባጭ ፍቅርን ለማሳየት መጣራቸውን በማስታወስ፥ በእጅ መንካትን፣ ምሕረትን እና አጽናኝ ቃላትን የመሳሰሉ ቀለል ያሉ ምልክቶችን በማሳየት ሕይወት እና በጎነት በሞት እና በክፋት ላይ የበላይነት እንዳላቸው የሚያሳዩ ምልክቶችን ያቀርቡ እንደ ነበር ተናግረዋል። ይህ ሐዋርያዊ መንፈስ በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ አገልግሎት መካከል መታየቱን ገልጸው፥ ራሳቸውን በአገልግሎት ማድከማቸው በመጨረሻ በረከት ወደሚፈስበት የብርሃነ ትንሳኤው እሑድ ላይ ደርሰዋል ሲሉ አስረድተዋል።

በድርቅ ወቅት መዝራት ልዩ እምነትን ይጠይቃል

ብፁዕ ካርዲናል ባልዳዛር አሁን የምንገኝበት ወቅት የብቸኝነት እና የፍርሃት እንዳልሆነ፥ “ይልቁኑ ቤተ ክርስቲያን ለጠንካራ ታማኝነት የተጠራችበት ጊዜ እንደሆነ፥ በሚያታልሉ እና እርግጠንነት በሌላቸው ወይም በዓለማዊ ፈተናዎች ሳትሸነፍ አዲስ ሰማይን እና አዲስ ምድርን እንድትቀበል የተጠራችበት ጊዜ ነው” ሲሉ አስረድተዋል።

እውነተኛ ታማኝነት ማለት በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የተጀመሩትን የተሐድሶ መንገዶችን በመለየት በድፍረት መከተል ማለት እንደሆነ አስረድተው፥ ፍርሃትን እና የሐሰት መግባባቶችን በሚቃወም በወንጌላዊ ርኅራኄ እና አንድነት ላይ የተመሠረተ አመራር መፈለግ ማለት እንደሆነም አክለው አስረድተዋል።

ብፁዕ ካርዲናል ባልዳዛር ሬይና፥ በዮሐንስ ወንጌል ላይ በማስተንተን ባሰሙት ስብከታቸው፥ “በእርሻ ላይ የተዘራ እህል ፍሬ እንዲያፈራ መሞት አለበት” የሚለውን የኢየሱስ ክርስቶስ ሞት እና የአዳኝነት ትንሳኤን የሚገልጽ የስንዴ ዘር ምሳሌን ጠቅሰዋል።

ክርስቲያኖች ኢየሱስ ክርስቶስን በመከተል አዲስ ሕይወት ለማግኘት እንደ “ዘር” መቀበር እንዳለባቸው ተናግረዋል፥ በመዝሙረ ዳዊት መጽሐፍ እንደተጠቀሰው፥ በድርቅ ወቅት መዝራት ልዩ እምነትን እንደሚጠይቅ፥ ጭራሽ ተስፋ የሌለ በሚመስል ሁኔታ ውስጥ እንኳን እምነት ሊኖር እንደሚገባ አሳስበዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ባዘጋጁት መንገድ ጉዞን መቀጠል

ብጹዕ ካርዲናል ባልዳዛር የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የመጨረሻዎቹን ይፋዊ አገልግሎቶችን ከዘር ምሳሌ ጋር በማመሳሰል፥ ቅዱስነታቸው የዘሩት ዘር ነፍሱን ለበጎቹ አሳልፎ የሰጠው የመልካሙ እረኛ የኢየሱስ ክርስቶስ ተልዕኮ ህያው ምስክርነት እንደሆነ አስረድተዋል።

ብፁዕ ካርዲናል ባልዳዛር ሬይና በስብከታቸው መደምደሚያ፥ የሮም ከተማ ነዋሪዎች ጠባቂ የሆነች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም፥ ቤተ ክርስቲያን በሟቹ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በጀመሩት መንገድ ለመቀጠል ድጋፍ እንድትሆናቸው ተማጽነው፥ ለምእመናን ባቀረቡት የማበረታቻ ቃልም፥ ሞት መጨረሻ ሳይሆን ነገር ግን ትንሳኤ የሚገለጥበት እንደሆነ በማሳሰብ ስብከታቸውን አጠቃልለዋል።

 

29 Apr 2025, 11:13