በነፋስ ኃይል ሲገለጡ ከሚታዩ የወንጌል ገፆች ጋር ለር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ስንብት ተደረገ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ከሃያ ዓመታት በፊት ማለትም በመለኮታዊ ምሕረት እሑድ ዋዜማ መጋቢት 30/1997 ዓ. ም. ማረፋቸው ይታወሳል። ከሃያ ዓመታት በኋላ በተመሳሳይም በመለኮታዊ ምሕረት በዓል ዋዜማ ማለትም ቅዳሜ ሚያዝያ 18/2017 ዓ. ም. በሺዎች የሚቆጠሩ ምዕመናን በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ተገኝተው ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የመጨረሻ ስንብት አድርገዋል።
ገጾቹ ቀስ በቀስ በነፋስ የሚገለጡት የቅዱስ ወንጌል መጽሐፍ ከእንጨት በተሰራ የአስከሬን ሳጥን ላይ ተቀምጦ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ይታይ ነበር።
የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የቀብር ሥነ-ሥርዓት እጅግ ጥልቅ እና ልብ የሚነካ ነበር። የመጨረሻቸው መሆኑን ሳያውቁ በብርሃነ ትንሣኤ እሑድ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ የነበሩ የእግዚአብሔር ሕዝቦች ቅዱስነታቸውን በመጨረሻው የምድራዊ ጉዞአቸው አጅበዋቸዋል።
በቅዱስነታቸው የቀብር ሥነ-ሥርዓት ዕለት በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ የተገኙት ርዕሰ መስተዳድሮች እና ታላላቅ መሪዎች ብቻ ሳይሆን ነገር ግን የታዳጊዎች ኢዮቤልዩን ለማክበር እና እግረ መንገዳቸውንም ቅዱስነታቸውን ሊጎበኙ የተመኙ በርካታ ወጣቶችም ነበሩ።
በተጨማሪም በርካታ የሌሎች አብያተ ክርስቲያናት ተከታዮች እና የተለያዩ ሃይማኖቶች ተወካዮች በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ አደባባይ ደረጃዎች ላይ ተሰብስበው ነበር። ለወንጌል ታማኝ የነበሩትን እና ዘወትር ወንድማማችነትን መስበክ ያላቆሙ፣ ሆስፒታል ገብተውም ጦርነት እንዲያቆም ጥሪ ሲያቀርቡ የነበሩትን እረኛ ሁሉም በአንድነት ተሰናብተዋል።
የቅዱስነታቸውን የቀብር ሥነ-ሥርዓት መስዋዕተ ቅዳሴ የመሩት ብፁዕ ካርዲናል ጆቫኒ ባቲስታ በዕለቱ ባሰሙት ስብከት ውስጥ በተለይ ሁለት ነጥቦች አድናቆት ተችሮላቸዋል። የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ተልዕኮ ዋና መሪ የሆነው፥ “ቤተ ክርስቲያን በሮቿ ሁል ጊዜም ክፍት የሆነ የሁሉም ቤት ናት” በማለት ደጋግመው መናገራቸውን ገልጸዋል።
በፖርቱጋን መዲና ሊዝበን በተከበረው የዓለም ወጣቶች ቀን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ “አንድነት፣ መተባበር፣ ኅብረት” በማለት መናገራቸውን ብፁዕ ካርዲናል ጆቫኒ ባቲስታ፥ ቅዱስነታቸው እነዚህን ቃላት በመናገር፥ “እጆቹን ዘርግቶ ሊቀበለን ከሚጠብቀን ከእግዚአብሔር ፍቅር ምንም እና ማንም ሊለየን አይችልም” በማለት ማስረዳታቸውን አስታውሰዋል።
ነፍስሔር ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለተናቁት፣ ለድሆች እና ለትሑታን ቅድሚያን በመስጠት በሮቿ የተከፈቱ ቤተ ክርስቲያንን ለመገንባት መፈለጋቸውን ገልጸው፥ ታላቅ ክብር ከሚሰጧቸው መካከል አንዱ በሆነው በእመቤታችን ቅድስት ማርያም ታላቁ ባዚሊካ ውስጥ በሚገኝ የሮም ከተማ ጠባቂ እመቤታችን ማርያም ምስል አጠገብ ከመቀመጡ በባዚሊካው ደጃፍ ተገኝተው አስከሬናቸውን የተቀበሉት ድሆች እና የተቸገሩት ሰዎች እንደ ነበሩ አስታውሰዋል።
በቀብር ሥነ ሥርዓቱ ላይ የተሰበሰቡት በሺዎች የሚቆጠሩ ምዕመናንም ካርዲናል ሬ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለሰላም ያላሰለሰ ጥረት ማድረጋቸው በማስታወስ ያቀረቡትን ስብከት አድንቀዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ “ሰዎች እንዲያመዛዝኑ” በማለት ላቀረቡት ግብዣ ምዕመናኑ የተሰማቸውን ደስታ ገልጸው፥ ጦርነት በሰዎች ላይ ሞትን፣ በመኖሪያ ቤቶች፣ በሆስፒታሎች እና በትምህርት ቤቶች ላይ ጥፋትን ብቻ የሚያስከትል በመሆኑ የሰላም መፍትሄን ለማግኘት እውነተኛ ድርድር እንደሚያስፈልግ፣ ጦርነት ዓለም ከበፊቱ የበለጠ የከፋ እንዲሆን የሚያደርግ ለሁሉም ሰው ሐዘን እና ሽንፈትን ነው” ማለታቸውን አስታውሰዋል።
ቅዳሜ ሚያዝያ 18/2017 ዓ. ም. የቀብር መስዋዕተ ቅዳሴ ከመጀመሩ በፊት የአሜሪካው ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ እና የዩክሬኑ አቻቸው ዜለንስኪ ለተወሰኑ ደቂቃዎች ተገናኝተው ተወያይተዋል። ከዚህ ውይይት አዎንታዊ ነገር እንደሚመጣ፣ ለሰላም የጸለየውን የአሲሲ ቅዱስ ፍራንችስኮስ ስም ለመጀመሪያ ጊዜ የወሰዱት፣ የሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ ተተኪ የሆኑት የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የመጨረሻው የሰላም ጥሪ እውን እንደሚሆን ተስፋ እናደርጋለን” ሲል የቫቲካን መገናኛዎች ርዕሠ አንቀጽ ዝግጅት ክፍል ዳይሬክተር አቶ አንድሬያ ቶርኔሊ ርዕሠ አንቀጹን ደምድሟል።