በዳካር የተዘጋጀው የሃይማኖታዊ ዲፕሎማሲ ሲምፖዚየም በዳካር የተዘጋጀው የሃይማኖታዊ ዲፕሎማሲ ሲምፖዚየም  

ሊቀ ጳጳስ አቡነ ጋላገር፥ ሴኔጋል ሃይማኖቶች በሰላም አብሮ የመኖር ተምሳሌት ናት ሲሉ አወደሱ

የቫቲካን የውጪ ሃገራት እና የዓለም አቀፍ ድርጅቶች ግንኙነት ክፍል ሃላፊ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ፖል ሪቻርድ ጋላገር፥ በዳካር የሚገኝ የቼክ አንታ ዶፕ ዩኒቨርሲቲ ላዘጋጀው የሃይማኖታዊ ዲፕሎማሲ ሲምፖዚየም መልዕክት ልከዋል። ሊቀ ጳጳሳ አቡነ ጋላገር ለሲምፖዚየሙ ተካፋዮች በላኩት መልዕክት፥ ሃይማኖቶች ለዲፕሎማሲ ተግባራት ያበረከቱትን አስተዋፅዖ አስታውሰው፥ ሴኔጋል ሃይማኖቶች በሰላም አብሮ የመኖር ተምሳሌት መሆኗን በመጥቀስ አወድሰዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በዳካር የሚገኘው የቼክ አንታ ዶፕ ዩኒቨርሲቲ “ሃይማኖታዊ ዲፕሎማሲ” በሚል መሪ ሃሳብ ከመጋቢት 29-30/2017 ዓ. ም. የዘጋጀው ዓለም አቀፍ ሲምፖዚየም ዋና ዓላማ፥ “ሃይማኖቶች በሰላም ግንባታ እና ግጭትን በማስታረቅ ረገድ ላይ ያላቸውን ሚና በማስመልከት የተዋቀረ አካዳሚያዊ እና መንፈሳዊ ጥረትን ማብራራት” ሲሆን፥ ዩኒቨርሲቲው በዳካር ለሚገኝ የቅድስት መንበር ሐዋርያዊ እንደራሴ ጽሕፈት ቤት ተወካይ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ዋልድማር ሶመርታግን መጋበዙ ታውቋል።

ሲምፖዚየሙ ሃሳባቸውን ለተሳታፊዎች ያካፍሉ በርካታ ተናጋሪዎችን የጋበዘ ሲሆን፥ ከእነዚህም መካከል መቀመጫቸውን ዳካር ውስጥ ያደረጉ አምባሳደሮች፣ የአውሮፓ የአይሁድ መምህራን ጉባኤ ምክትል ፕሬዝዳንትን ሞሼ ሌዊን ጨምሮ የባህላዊ ሃይማኖት ተወካዮችንም ማሳተፉ ታውቋል።

ጉባኤውን ይከፍታሉ ተብለው ሲጠበቁ የነበሩት የቫቲካን የውጪ ሃገራት እና የዓለም አቀፍ ድርጅቶች ግንኙነት ክፍል ሃላፊ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ፖል ሪቻርድ ጋላገር በጉባኤው ላይ መገኘት ባይችሉም ነገር ግን ሴኔጋል ሃይማኖቶች በሰላም አብሮ የመኖር ባሕልን በማስከበር ረገድ ላደረገችው ጥረት አመስግነው፥ ቅድስት መንበር ሃይማኖታዊ ዲፕሎማሲን እንዴት እንደምትረዳው በመልዕክታቸው አስረድተዋል።

ሴኔጋል የምትከተለው የሃይማኖቶች አብሮ የመኖር ሞዴል

ዘንድሮ የካቲት 15 ቀን ቫቲካንን የጎበኙ የሰላም እና የውይይት አቀንቃኝ ታዋቂውን የባምቢሎር ካሊፋ ቲየርኖ አማዱ ባን ያስታወሱት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ፖል ሪቻርድ ጋላገር፥ “በተለያዩ ሃይማኖታዊ እና ባህላዊ ወጎች መካከል በሰላም አብሮ መኖር በሴኔጋል ውስጥ ትርጉም ያለው እውነታ ነው” ሲሉ በመልዕክታቸው መግቢያ ላይ አጽንዖት ሰጥተዋል።

ሊቀ ጳጳስ አቡነ ፖል ሪቻርድ ጋላገር፥ “በአንድ ቤተሰብ ውስጥ የሙስሊሞች፣ የካቶሊኮች፣ የፕሮቴስታንቶች እና የባህላዊ ሃይማኖት ተከታዮች በሚያስደንቅ ሁኔታ ተስማምተው የሚኖሩበትን የሴኔጋልን ሞዴል አወድሰው፥ ይህ ሁኔታ “በሃይማኖቶች መካከል የሚደረግ ውይይትን የሚያበረታታ እና ሊከበር የሚገባው ነው” ብለው፥ የባምቢሎር ካሊፋ ቲየርኖ አማዱ በቅርቡ ቫቲካንን በጎበኙበት ወቅት፥ “ሴኔጋል የሃይማኖቶች በሰላም አብሮ የመኖር ተምሳሌት ናት” ማለታቸውን ገልጸዋል።

የሃይማኖት ዲፕሎማሲ ለሰላም ያለው አስተዋፅኦ

ሊቀ ጳጳስ አቡነ ጋልገር አክለውም፥ “ዓለማችን ጊዜያዊ የብጥብጥ መቆም ብቻ ሳይሆን ዘላቂ ሰላምን፣ በፍትህ፣ በአብሮነት እና በእውነተኛ ሞራል ላይ የተመሠረተ ሰላምን ትፈልጋለች” ብለው፥ በዚህ አውድ ውስጥ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ሃይማኖት የሰላም እንቅፋት ሳይሆን ነገር ግን ወሳኝ ምሰሶ መሆኑን በተጨባጭ ለማሳየት በንቃት ትጥራለች” ብለዋል።

የቫቲካን የውጪ ሃገራት እና የዓለም አቀፍ ድርጅቶች ግንኙነት ክፍል ሃላፊ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ፖል ሪቻርድ ጋላገር፥ ሃይማኖቶች ለዲፕሎማሲያዊ ተግባር የሚያበረክቱት አስተዋፅዖ፥ “ዲፕሎማሲያዊ ራዕይ በመንግሥት ልውውጥ ወይም በፖለቲካዊ ስምምነት ላይ የተገደበ ነው” ከሚለው በላይ እንደሆነ አስረድተዋል።

ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ስለ ሃይማኖታዊ ዲፕሎማሲ ያላትን ራዕይ በማስታወስ እንደተናገሩት፥ “በሃይማኖታዊ ወጎች በሚቀርቡት ልዩ ሥነ-ምግባራዊ እና ሞራላዊ አመለካከቶች ላይ የተመሠረተ ዲፕሎማሲያዊ ተግባር እንደሆነ እና ይህም በመንግሥታት መካከል ባለው ግንኙነት ላይ ተጽዕኖን ማሳደር እንደሆነ አስረድተው፥ የሃይማኖታዊ ዲፕሎማሲ ኃይል በፖለቲካ ወይም በወታደራዊ ተጽዕኖ ውስጥ በጥቂቱ ቢታይም ይበልጥ የሚገለጠው የግለሰቦችን ልብ እና አእምሮ በመንካት ችሎታው ነው” ብለዋል።

ለወደፊቱ አዲስ ተነሳሽነት

በሴኔጋል የሚገኙ በርካታ ዲፕሎማቶችን በማሰባሰብ የተካሄደው የሁለት ቀናት ውይይቶች እጅግ ፍሬያማ እንደ ነበሩ ተገልጿል። የሊቀ ጳጳስ አቡነ ፖል ሪቻርድ ፖል ጋላገርን መልዕክት ለጉባኤው በንባብ ያሰሙት፥ በዳካር የቅድስት መንበር ሐዋርያዊ እንደራሴ ጽሕፈት ቤት ተወካይ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ዋልድማር ሶመርታግ፥ “ሴኔጋል ውስጥ ቤተ ክርስቲያን የምትናገረውን ሕዝቡ በትኩረት ይከታተላል” ሲሉ ተናግረው፥ ስብስባው ለወደፊቱ አዲስ መነሳሳትን እንደሚያመጣ አስረድተዋል።

በባዳካር በሚገኝ ቼክ አንታ ዶፕ ዩኒቨርሲቲ የተካሄደው ሲምፖዚየም ፍሬ እንደሚያፈራ ተሳታፊዎች አረጋግጠው፥ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ሶመርታግ ከባምቢሎር ኸሊፋ ጋር ባደረጉት የሃሳብ ልውውጥም፥ ሥራው ቀጣይነት ሊኖር እንደሚያስፈልገው በገለጹላቸው ጊዜ አዲስ ጉብኝቶችን ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን እና ወደ ሮም የመመለስ ፍላጎት እንዳላቸው መግለጻቸን ተናግረዋል።

በሴኔጋል የሃይማኖቶች ውይይቶች ተጠናክረው ለመቀጠላቸው ትልቁ ምልክት፥ በዳካር የሚገኘው የቅድስት መንበር ሐዋርያዊ እንደራሴ ጽሕፈት ቤት ተወካይ ለሆኑት ለሊቀ ጳጳስ አቡነ ዋልድማር ሶመርታግ የዚያራ ባምቢሎር ካሊፋ ያቀረቡላቸው ግብዣ ሲሆን፥ ይህም በሺዎች የሚቆጠሩ ሙስሊሞች እና የአካባቢያቸው የሃይማኖት መሪዎች በየዓመቱ ወደሚሰበሰቡበት ቅዱስ ቦታዎች የሚደረግ ንግደት እንደሆነ ታውቋል።

 

12 Apr 2025, 17:08