ካርዲናሎች በስድስተኛው ጠቅላላ ጉባኤ ላይ የቅድመ ጉባኤ ቅዳሴን እንደሚያቀርቡ ገለጹ

የብጹዓን ካርዲናሎች ኅብረት ማክሰኞ ዕለት ስድስተኛውን ጠቅላላ ጉባኤን ባካሄዱበት ወቅት ዝግ ጉባኤን፥ “ኮንክላቭ” ከመጀመራቸው ቀደም ብሎ የሚያሳርጉትን መስዋዕተ ቅዳሴ እና ወደ ሲስቲን ጸሎት ቤት ለመግባት የሚያደርጉትን ኡደት የሚገልጽ መርሃ-ግብር ይፋ አድርገዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ብጹዓን ካርዲናሎች ማክሰኞ ሚያዝያ 21/2017 ዓ. ም. ጠዋት በአዲሱ የቅዱስ ሲኖዶስ አዳራሽ ባካሄዱት ስድስተኛው ጠቅላላ ጉባኤ ላይ 124 ብፁዓን መራጭ ካርዲናሎችን ጨምሮ 183 ካርዲናሎች ተገኝተዋል። በጠቅላላ ጉባኤው ላይም ወደ 20 የሚጠጉ ካርዲናሎች ንግግር አድርገዋል።

አኅጉሮቻቸውን እና የትውልድ አካባቢዎቻቸውን መሠረት በማድረግ የተደረጉ ንግግሮች የቤተ ክርስቲያኒቱን ተግዳሮቶች እና የምትሰጣቸውን ምላሾች በማስመልከት መሪ ሃሳቦችን አቅርበዋል።

የቅድስት መንበር መግለጫ ክፍል ዳይሬክተር ማትዮ ብሩኒ ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት፥ ሁለት መራጭ ካርዲናሎች በጤና ምክንያት በጉባኤው ላይ እንደማይገኙ አስታውቀዋል።

በተናጥል ብፁዕ ካርዲናል ጆቫኒ አንጀሎ ቤቹ ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ፈቃድ በመገዛት በዝግ ጉባኤው ላይ እንደማይሳተፉ አስታውቀዋል።

የብጹዓን ካርዲናሎች ጠቅላላ ጉባኤ ሰኞ ሚያዝያ 20/2017 ዓ. ም. ባካሄደው ስብሰባ በቅርቡ የር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ዕረፍት አስመልክቶ በተደረጉት ዝግጅቶች ላይ ለተሳተፉት እና ለመላው ዓለም የምስጋና መልዕክት ለመላክ መወሰናቸው ይታወሳል።

የመራጭ ካርዲናሎች ዝግ ጉባኤ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ2013 ዓ. ም. የተካሄደውን ጨምሮ በቀደሙት ጉባኤዎች መሠረት ሚያዝያ 29/2017 ዓ. ም. እንደሚጀምር ተገልጿል።

የብጹዓን ካርዲናሎች ኅብረት መሪ ብፁዕ ካርዲናል ጆቫኒ ባቲስታ ሬ በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ከጠዋቱ አራት ሰዓት ላይ የሚቀርበውን የቅድመ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ምርጫ (ፕሮ ኤሊገንዶ ፓፓ) መስዋዕተ ቅዳሴን ይመራሉ።

የመራጭ ካርዲናሎች ዝግ ጉባኤ ሚያዝያ 29/2017 ዓ. ም. ከጠዋቱ አራት ሰዓት ተኩል ላይ በቅዱስ ጳውሎስ ጸሎት ቤት በሚቀርብ የጸሎት ሥነ-ሥርዓት በይፋ ይጀመራል።

ከጸሎት ሥነ-ሥርዓቱ በኋላ መራጭ ካርዲናሎች በዑደት ወደ ሲስቲን ጸሎት ቤት ከማምራትቸው በፊት ወደ ቅዱሳን ዘንድ የሚቀርብ ጸሎት “ሊታኒ” በኅብረት ይደግማሉ።

 

30 Apr 2025, 17:10