የሱዳን የእርስ በርስ ጦርነት ተባብሶ በቀጠለበት በአሁኑ ወቅት በደቡብ ሱዳን እንደገና ግጭት ይነሳል የሚል ስጋት አይሏል
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
ኒኮላስ ሃይሶም የተባሉ የተባበሩት መንግስታት ባለስልጣን በሃገሪቷ እየታየ ያለውን ሁኔታ “አደገኛ” በማለት የገለጹ ሲሆን፥ ፕሬዚደንት ሳልቫ ኪር እና ምክትል ፕሬዝዳንት ሪክ ማቻር ከግል ጥቅም ይልቅ የህዝባቸውን ፍላጎት እንዲያስቀድሙ አሳስበዋል።
ደቡብ ሱዳን ከዓመታት ደም አፋሳሽ ግጭት በኋላ እ.አ.አ በ2011 ዓ.ም. ከሱዳን ነፃነቷን አግኝታ የነበረች ቢሆንም በ 2013 ዓ.ም. ሀገሪቱ መልሳ ወደ እርስ በርስ ጦርነት ልትገባ ችላለች።
በሌላ በኩል የሱዳን ጦር ሰራዊት በካርቱም የሚገኘውን ፕሬዚዳንታዊ ቤተ መንግስት በመቆጣጠር ከፈጣን ድጋፍ ሰጭ ሃይሎች ጋር እያካሄደ ባለው የእርስ በርስ ጦርነት ከፍተኛ ድል ማስመዝገቡ እየተነገረ ይገኛል።
የእርስ በእርስ ጦርነቱ እንደ ጀመረ የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ዋና ከተማዋን በመቆጣጠሩ በሀገሪቱ ጦር የሚመራው መንግሥት መቀመጫውን ቀይ ባህር ድንበር ላይ ወደሚገኘው ፖርት ሱዳን ለማዞር ተገዷል።
አርብ እለት የአገሪቱ ጦር የፕሬዚዳንቱን ቤተ መንግሥት በድጋሚ ከተቆጣጠረ እና በፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ስር የነበሩ ሌሎች የመንግሥት ተቋማትን ካስለቀቀ በኋላ በከተማዋ ያለውን ኃይል እያጠናከረ መጥቷል።
የሱዳን የኢንፎርሜሽን ሚኒስትር ካሊድ አል-አይሰር የሱዳን ጦር ሰራዊት ያገኘውን ስኬት ያረጋገጡ ሲሆን፥ የሃገሪቱ ባንዲራ ከፍ ብሎ መውለብለቡን፣ ቤተ መንግሥቱን መቆጣጠራቸውን እና ድሉ እስኪጠናቀቅ ድረስ ጉዞው እንደሚቀጥል ገልጸዋል።
የተባበሩት መንግስታት የህጻናት ኤጀንሲ ሃላፊው በሱዳን እየተካሄደ ያለውን ግጭት ‘በዓለም ትልቁ የሰብአዊ ቀውስ’ ሲሉ የገለጹ ሲሆን፥ በዚህም በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መገደላቸውን፣ ሚሊዮኖች መፈናቀላቸውን፣ ከዚህም ባለፈ በተከሰተው ረሃብ ምክንያት አንዳንድ ቤተሰቦች ለመኖር ሲሉ ሳር ለመብላት መገደዳቸውን ተናግረዋል።
በሃገሪቱ ለዓመታት የዘለቀው አለመረጋጋት የመነጨው በ 2011 ዓ.ም. ለረዥም ጊዜያት ሃገሪቷን ሲመሯት የነበሩት ፕረዚዳንት ኦማር አልበሽር ከስልጣን መወገዳቸውን ተከትሎ እንደሆነ መረጃዎች ያሳያሉ።
በ 2013 ዓ.ም. በጄኔራል አብደል ፈታህ አል-ቡርሃን እና በመሀመድ ሃምዳን ዳጋሎ የተመራው ወታደራዊ መፈንቅለ መንግስት ወደ ዲሞክራሲ ሲደረግ የነበረውን አጭር ሽግግር አቅጣጫ የቀየረ ሲሆን፥ በ 2015 ዓ.ም. በመፈንቅለ መንግስት አድራጊዎቹ መካከል የነበረው ግጭት ተባብሶ በሱዳን ጦር ሰራዊት እና በፈጥኖ ደራሽ ሃይሉ መካከል ጦርነት እንዲከሰት አድርጓል።
በእርስ በርስ ጦርነቱ በአጠቃላይ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሲገደሉ፣ ሚሊዮኖች ደግሞ ቤት ንብረታቸውን ጥለው ለመሰደድ የተገደዱ ሲሆን፥ በዚህም ወቅት ሁለቱም ወገኖች የሰብዓዊ መብት ጥሰት ክስ እንደቀረበባቸውም ተነግሯል።