በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ 10 ሚሊዮን የሚሆኑ ክርስቲያን ስደተኞች የመባረር አደጋ እንደተጋረጠባቸው ተገለጸ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
የአሜሪካ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ብጹአን ጳጳሳት ጉባኤ (USCCB) ከወንጌላውያን ብሄራዊ ማህበር፣ ከወርልድ ሪሊፍ እና ከዓለም አቀፍ የክርስትና ጥናት ማዕከል ጋር በመተባበር ባወጣው ዘገባ መሰረት በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ሊሻሩ የሚችሉ ጊዜያዊ ጥበቃ ያላቸውን ጨምሮ ከ 10 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ክርስቲያን ስደተኞች ከሃገሪቷ የመባረር አደጋ መጋለጣቸውን የገለጹ ሲሆን፥ ወደ 7 ሚሊዮን የሚጠጉ የዩናይትድ ስቴትስ ዜግነት ያላቸው ክርስቲያኖች ደግሞ የሚኖሩት በአንድ ቤተሰብ ውስጥ የመባረር አደጋ ላይ ካሉ ሰዎች ጋር እንደሆነ አብራርተዋል። የመባረር አደጋ ከተጋረጠባቸው ክርስቲያኖች መካከል 18 በመቶ የሚሆኑት ካቶሊኮች ሲሆኑ 6 በመቶው ደግሞ የወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት እና የተቀሩት የሌላ እምነት ተከታዮች እንደሆኑ ዘገባው ያሳያል።
የአንድ አካል ክፍል
“የአንድ አካል ክፍል” በሚል ርዕስ የወጣው ሪፖርቱ በአሜሪካ ውስጥ ለሚገኙ የክርስቲያን ጉባኤዎች፣ በተለይም በትራምፕ አስተዳደር ወቅት ከሃገር የማስወጣት ፖሊሲዎች እንደ አንድ የክርስቶስ አማኝ ርህራሄ በሚገባቸው የራሳቸው የሃይማኖት ማህበረሰብ አባላት ላይ ያለውን ተፅእኖ ግንዛቤ ለማስጨበጥ ያለመ ነው ተብሏል።
የስደት ጉዳዮች ኮሚቴ ሊቀ መንበር በሆኑት የኤል ፓሶ ጳጳስ ብጹእ አቡነ ማርክ ጄ የተፈረመበት የሪፖርቱ መግቢያ ደብዳቤ እንደሚገልጸው “እግር የሚያዳክም ሕመም ካለበት እጅ ምንም ጉዳት ሳይደርስበት ሥራውን ማከናወን እንደማይችል ሁሉ የቤተክርስቲያኑ አንድ ክፍል በሚሰቃይበት ጊዜ ሁሉም አብረው ስቃዩን ለመጋፈጥ ይገደዳሉ” በማለት አሳስቧል።
20 ሚሊዮን ሰዎች በአሜሪካ የመባረር አደጋ ተጋርጦባቸዋል
ፈራሚ አካላቱ እንደገለጹት ይህ የሞራል ግዴታ የሆነው የርኅራኄ ተግባር ሃይማኖታዊ እምነታቸው ምንም ይሁን ምን፣ “በተፈጥሯዊ ክብር በእግዚአብሔር አምሳል ለተፈጠሩት ሁሉ ይገባል” (ዘፍጥረት 1፡27፣ ዘፍጥረት 9፡6፣ ያዕቆብ 3፡9) በማለት አብራርተዋል።
ሪፖርቱ ህጋዊ ሰነድ ያላቸውም ሆኑ የሌላቸው በርካታ ስደተኞች የክርስቲያን ማህበረሰብ ወሳኝ አባላት መሆናቸውን አጉልቶ በማሳየት፥ አብዛኛዎቹ በህጋዊ መንገድ የመጡ ሲሆኑ፣ ቁጥራቸው ቀላል የማይባሉት ደግሞ ህጋዊ ሁኔታ በሌለበት ወይም አስተማማኝ ሁኔታ ባለመኖሩ ምክንያት ከሃገሪቷ ለመባረር የተጋለጡ እንደሆኑ እና ይህ ተጋላጭነት በተለይ በፕሬዚዳንት ትራምፕ የጅምላ ከሃገር የማስወጣት ተግባርን ለመፈጸም ከገቡት ቃል አንፃር 20 ሚሊዮን ሰዎችን ኢላማ ያደረገ ነው ተብሏል።
ለርህራሄ የተደረገ ሃዋሪያዊ ጥሪ
ፈራሚዎቹ ሪፖርቱ ፓለቲካዊ ተማጽኖ አለመሆኑን ወይም ሁሉም ከሃገር የማስወጣት ተግባሮች ኢፍትሃዊ ናቸው እያለ እንዳልሆነ፥ ይልቁንም በአሁኑ ጊዜ በስደተኞች ላይ እየደረሰ ያለው ኢ-ፍትሃዊ እርምጃ በቤተክርስቲያናት፣ በቤተሰብ እና በማህበረሰቦች ላይ የሚያስከትለውን ጥልቅ መንፈሳዊ እና ተያያዥ መዘዞች ክርስቲያኖች እንዲገነዘቡ የተደረገ ሃዋሪያዊ ጥሪ ነው ብለዋል።
ከቀረቡት ጥልቅ ግንዛቤዎች ውስጥ አንዱ አብዛኛዎቹ በአሜሪካ ውስጥ የሚገኙ ሰነድ የሌላቸው ወይም የመባረር አደጋ ተጋላጭ የሆኑ ስደተኞች መካከል ቢያንስ በእነሱ ግንዛቤ ከአምስቱ ውስጥ አራቱ በእውነቱ ክርስቲያኖች እንደሆኑ ገልጸዋል።
ይህ ሪፖርት፥ ለመባረር በጣም የተጋለጡት የሩቅ እንግዶች እንዳልሆኑ ከዚህም ይልቅ የእምነት ባልንጀሮቻቸው፣ አልፎ ተርፎም የቁምስና ባልንጀሮቻቸው መሆናቸውን ያላወቁ ክርስቲያኖችን ሕሊና ለመቀስቀስ የታሰበ አስገራሚ አኃዛዊ መረጃ እንደሆነ አመላክተዋል።
ከዚህም ባለፈ ሪፖርቱ በመላ አገሪቱ ካሉት የካቶሊክ እና የፕሮቴስታንት አብያተ ክርስቲያናት የተውጣጡ ግለሰቦች ጉዳይ ጭምር የተደገፈ አኃዛዊ ትንታኔ የሚሰጥ ሲሆን፥ በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ከአሥራ ሁለት ክርስቲያኖች ውስጥ አንዱ ለስደት የተጋለጠ ወይም ለመባረር አደጋ ከተጋለጠው ጋር እንደሚኖር ያሳያል። ይህ በመሆኑም የኢሚግሬሽን ማስፈጸሚያ ትእዛዙ የህዝብ ፖሊሲ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን ቀጥተኛ የሃዋሪያዊ ተልዕኮ ስጋትም እንደሆነ ገልጸዋል።
ሕግን፣ ፍትሕን እና ምሕረትን ማመጣጠን
ሪፖርቱ በሮሜ 13 ላይ የተጠቀሰውን መጽሃፍ ቅዱሳዊውን የመንግስት ስልጣንን የማክበር ግዴታን (ሮሜ 13) እውቅና የሚሰጥ ሲሆን፥ ያም ሆኖ ግን ፍትህን እና ርህራሄን ለሚያካትተው የስደት ህግ ሚዛናዊ አቀራረብን እንደሚደግፍ ተነግሯል።
አብያተ ክርስቲያናቱ ከሃገር ማስወጣት ህግን የማስከበር አንዱ መንገድ እንደሆነ በመግለጽ፥ ነገር ግን ብቸኛው ወይም ሁሌም በጣም ሥነ ምግባር የተሞላበት እንዳልሆነ የጠቀሱ ሲሆን፥ ለብዙ ስደተኞች ህጋዊ ሁኔታን የሚያመቻቹ የፖሊሲ አማራጮች እንዳሉ እና እነዚህ በፖለቲካዊ ክርክሩ ውስጥ በቁም ነገር መታየት እንዳለባቸው ገልጸዋል።
ለተግባራዊ እርምጃ የተደረገ ጥሪ
የአቢያተ ክርስቲያናቱ ደብዳቤ የሚያጠቃልለው በዚህ እርግጠኝነት በሌለበት እና ፍርሀት በነገሰበት ጊዜ ውስጥ ሚናቸውን እንዲመረምሩ ለአሜሪካውያን ክርስቲያኖች ጠንካራ መልዕክት በማስተላለፍ ሲሆን፥ ከመጽሃፍ ቅዱስ ክፍል የዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ 13 ቁጥር 35ን በመጥቀስ፥ እርስ በርስ መዋደድ የደቀመዝሙርነት ዋነኛ ምልክት እንደሆነ፣ ይህም ወደ ተጨባጭ ተግባራት መተርጎም እንዳለበት እና መከራ በሚደርስበት ጊዜ፣ በተለይም ያ መከራ በክርስቶስ አንድ አካል የሆኑ ባልንጀሮችን በሚነካበት ጊዜ ክርስቲያኖች እንዲጸልዩ፣ እንዲሟገቱ እና ተግባራዊ እርምጃዎችን እንዲወስዱ ጥሪ አቅርበዋል።