ፈልግ

ካርዲናል ብርሃነየሱስ ሱራፌል፣ ሊቀ ጳጳሳት ዘ ካቶሊካዊያን፣ የኢትዮጲያ ካቶሊክ ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዚዳንት ካርዲናል ብርሃነየሱስ ሱራፌል፣ ሊቀ ጳጳሳት ዘ ካቶሊካዊያን፣ የኢትዮጲያ ካቶሊክ ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዚዳንት  

የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የሀዘን መግለጫ!

በስመ አብወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን፡፡ በክርስቶስ የተወደዳችሁ ብፁዓን ጳጳሳት
ክቡራን ካህናት፤ ገዳማውያንና ገዳማውያት ካቶሊካውያንምዕመናን እና በጎ ፈቃድ
ላላቸው ሰዎች ሁሉ ዛሬ እኛ የኢትዮጵያ ካቶሊካውያን እጅግ አሳዛኝ የሆነውን የቅዱስ አባታችን የብጹዕ ወቅዱስ ርዕሰሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቼስኮስን ከዚህ ዓለም ድካም ማረፍ ሰምተናል።  እግዚአብሔር አምላክ የሚወዳቸውን እኚህን ታላቅ አባታችን በጌታችን መድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ ማግስት ወደዘለዓለማዊ ማረፊያው ወስዷቸዋል። ቅዱስ አባታችን ባለፉት ወራት በደረሰባቸውከባድ ህመም በህክምና ሲረዱ ቆይተዋል እኛም በጸሎት ህብረት አብረናቸው ነበርን። በቫቲካን በሚገኘውም ቅድስት መንበራቸው ተመልሰው ህክምናቸውን ሲከታተሉ ቆይተው ነበር። በትናትናውም ዕለት የትንሣኤ በዓል መልካም ምኞታቸውን እና ለዓለም ሰላም ያላቸውን ፍላጎትበቫቲካን ቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ በመገኘት ለመላው ምዕመናን አስተላልፈዋል።
ዛሬ ጠዋት በሮምየሰዓት አቆጣጠር 7፡35 (በኢትዮጵያ የሰዓት አቆጣጠር 2፡35) ላይ የቅድስት መንበር እረኛ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳትፍራንቼስኮስ ወደ አባታቸው እግዚአብሔር አብ ቤት ተመልሰዋል። ቅዱስ አባታችን ሕይወታቸውን በሙሉ ለጌታ እና ለቤተክርስቲያን አገልግሎት የሰጡ ነበሩ።  የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ እውነተኛ ደቀ መዝሙርበመሆን ላሳዩት የሕይወት ምሳሌነት ታላቅ ምስጋና እየሰጠን የብፁዕ ወቅዱስ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቼስኮስን ነፍስ ለአንዱና ለቅድስት ሥላሴ ማለቂያ የሌለው መሐሪ ፍቅር በአደራ እንሰጣለን። ቅዱስነታቸው ጌታችንመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ የመሰረታትን ከ1.4 ቢሊዮን በላይ ምዕመናን ያሏትን ቤተክርስቲያን በክህነት፣በሊቀጳጳስነት፣ በካርዲናልነት እንዲሁም በቅድስት መንበር እረኝነት በርካታ ሐዋርያዊ አገልግሎቶችን ያበረከቱ ነበሩ። የኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን የጳጳሳት ጉባኤ በድጋሚ የተሰማንን ጥልቅሀዘን እየገለጽን በቅዱስ አባታችን የህመም ወቅት በጽሎት አብራችሁን ለነበራችሁ ካቶሊካውያን
እና በጎ ፍቃድ ያላችሁ ወገኖች ሁሉ እግዚአብሔር ይስጥልን እንላለን። ዛሬም እኛ በኢትዮጵያ የምንገኝ ካቶሊካውያን እና በጎፈቃድ ያላችሁ ወገኖች ሁሉ ለቅዱስ አባታችን ዘለዓለማዊ እረፍት በጸሎት አብራችሁን እንድትሆኑ ጥሪ እናቀርባለን።  የቅዱስነታቸውን ህልፈተ ሕይወት አስመልክቶ በሀገራችን እንዲሁም በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚከናወኑ የሥርዓተ ቀብር እና ሌሎች መርሃግብሮችን በተከታታይየምናሳውቅ መሆኑን እንገልጻለን።

ጌታ ሆይ ለሞቱት ሰዎች የዘለዓለም ሕይወትንስጣቸው የማያልቀውን ብርሃንህን አብራላቸው በሰላም አሳርፋቸው
አሜን!

21 Apr 2025, 20:14