ፈልግ

ዩክሬን መዲና ኪየቭ ውስጥ የቀረበ የአብያተ ክርስቲያናት የመስቀል መንገድ ጸሎት ዩክሬን መዲና ኪየቭ ውስጥ የቀረበ የአብያተ ክርስቲያናት የመስቀል መንገድ ጸሎት   (ANSA)

አብያተ ክርስቲያናት የመስቀል መንገድ ጸሎት በኅብረት አቀረቡ

በዩክሬን የቅድስት መንበር ሐዋርያዊ እንደራሴ ጽሕፈት ቤት ተወካይ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ቪስቫልዳስ ኩልቦካስ የሕማማት ሳምንት ከመግባቱ ቀደም ብሎ ዓርብ ሚያዝያ 3/2017 ዓ. ም. በኪየቭ የመሩት የአብያተ ክርስቲያናት የመስቀል መንገድ ጸሎት ጥልቅ ትርጉም ያለው መሆኑን ለቫቲካን የዜና አገልግሎት ገለጹ።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በጦርነት በምትሰቃይ ዩክሬን መዲና ኪየቭ ውስጥ ከታሪካዊው ቅድስት ሶፊያ ካቴድራል ፊት ለፊት ከአብያተ ክርስቲያናት የመጡ ምዕመናንን፣ የቀድሞው እስረኞችን እና የጦር ጉዳተኞችን ያሳተፈ የመስቀል መንገድ የጸሎት ሥነ-ሥርዓት በዩክሬን መዲና ኪየቭ ውስጥ ተፈጽሟል።

“በዩክሬን ውስጥ ሰላም እንዲመጣ እና የጦር እስረኞች እንዲፈቱ የቀረበ የመስቀል መንገድ ጸሎት” በሚል ርዕሥ የጦር እስረኞችን፣ የጦር ጉዳተኞችን፣ ሐዘን ላይ የሚገኙ ዘመዶቻቸውን እና በጦርነቱ ምክንያት የጠፉበትን በመጠባበቅ ላይ የሚገኙትን ጨምሮ ከልዩ ልዩ የክርስትና እምነቶች፥ ከግሪክ ካቶሊክ እና ከሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያናት፣ ከኦርቶዶክስ እና ከፕሮቴስታንት አብያተ ክርስቲያናት የመጡ ምዕመናንን ያሳተፈ የመስቀል መንገድ ጸሎት ሥነ-ሥርዓት ተፈጽሟል።

መርሃ ግብሩን ያዘጋጀው፥ “ዓለም አቀፍ የሴቶች ንቅናቄ ለቤተሰብ እሴት” በሚል መጠሪያ የሚታወቅ እንቅስቃሴ ሲሆን፥ ጸሎቱን የመሩት፥ በዩክሬን የቅድስት መንበር ሐዋርያዊ እንደራሴ ጽሕፈት ቤት ተወካይ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ቪስቫልዳስ ኩልቦካስ ናቸው። በጸሎቱ አስፈላጊነት እና ባያዘው መንፈሳዊ ትርጉም ላይ በማስተንተን ከቫቲካን የዜና አገልግሎት ጋር ቃለ ምልልስ ቅድርገዋል።

“በዓለም አቀፍ የሴቶች ንቅናቄ ለቤተሰብ እሴት” የተባለ ማኅበር ያዘጋጀው የጋራ የመስቀል መንገድ የጸሎት ሥነ-ሥርዓት እጅግ ልብ የሚነካ እንደ ነበር የገለጹ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ቪስቫልዳስ፥ በዩክሬን እየተካሄደ ባለው ጦርነት ሳቢያ እያንዳንዱ ቤተሰብ አንድ ሰው እንዳጣ፥ የጦር እስረኛ እንደሆነበት፣ እንደቆሰለበት፣ ወይም በጦር ግንባር እንደሚገኝ መናገር እንደሚቻል አስረድተዋል።

አብዛኛዎቹ ቤተሰቦች ባይፈልጉትም እራሳቸውን በጦርነቱ ውስጥ ማግኘታቸውን ገልጸው፥ ማኅበሩ የመስቀል መንገድ ጸሎት ሥነ-ሥርዓት ማዘጋጀቱ ያስደሰታቸው መሆኑን ተናግረዋል። ትርጉም ያለው ሥነ-ሥርዓትም እንደ ነበር እና በኪየቭ በሚገኘው እና የዩክሬን ብሔራዊ ቤተ መቅደስ በሆነው ጥንታዊ የቅድስት ሶፊያ ካቴድራል ዙሪያ የልዩ ልዩ አብያተ ክርስቲያናት ተወካዮች፥ የግሪክ ካቶሊክ፣ የሮማ ካቶሊክ እና የኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት ካህናት፣ ፕሮቴስታንቶች እና የሌሎች አብያተ ክርስቲያናት ተወካዮች መገኘታቸውን ተናግረዋል።

የጸሎት ሥነ-ሥርዓቱ እናቶች እና ሚስቶች በጦር ሜዳ ለወደቁት ዘመዶቻቸው ሲያዝኑ እና ከቆሰሉት እና የጦር ምርኮኛ ከሆኑት ዘመዶቻቸው ጋር ለመገናኘት የሚፈልጉ ሰዎችን ያሰባሰበ መሆኑን ገልጸው፥እነዚህ ምዕመናን የሕማማት ሳምንትን ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር በጸሎት ለመጀመር ፈለገው ልምዳቸውን እና ሕመማቸውን ከአዳኙ ኢየሱስ ክርስቶስ ጋር በመሆን በኅብረት ጸሎት ማቅረባቸውን አስረድተዋል።

የጸሎት ሥነ-ሥርዓቱን ለመፈጸም ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ያውቁ እንደ ነበር የገለጹት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ቪስቫልዳስ፥ ሁሉም የመስቀል መንገዱ ማረፊያዎች የኢየሱስ ክርስቶስን ስቃይ የሚያስታውሱ፣ ጸሎቱን የሚያቀርቡ ሰዎችም የኢየሱስ ክርስቶስን ስቃይ በግል ሕይወታቸው የተለማመዱ እንደ ነበሩ ገልጸው፥ ኢየሱስ ክርስቶስ እንደ ተፈረደበት የሚገልጸውን የመጀመርያውን ምዕራፍ አስተንትኖ ያቀረበው፥ መስቀል የተሸከመው፣ እግሩን እና ክንዱን የተቆረጠ የቀድሞ የጦር እስረኛ እንደ ነበር አስታውሰዋል።

ኢየሱስ ክርስቶስ መስቀሉን ለመሸከም እንደተቀበለ የሚገልጸውን የሁለተኛውን ምዕራፍ አስተንትኖ ያቀረበችው፥ የቀድሞው የጦር እስረኛ ሚስት እንደ ነበረች አስታውሰው፥ የባሎቻቸው መታሰር ለእያንዳንዷ ሚስት መከራ ነው” ሲሉ አስረድተዋል። የኢየሱስ ክርስቶስን ሞት በሚያስታውስ ምዕራፍ ላይ ያስተነተነው የዩክሬን ጦር ሠራዊት የሕክምና ባለሞያ ሲሆን፥ “ይህም በየዕለቱ በጦር ግንባር የሚዋደቁ ወታደሮችን የሚያገኛቸው ስለሆነ ነው” ብለዋል።

በሕይወታችን ውስጥ እንደዚህ ዓይነት ልምዶች ሲኖሩን ቀድሞውንም ከኢየሱስ ክርስቶስ ሕማማት ጋር የሚመሳሰሉ በመሆኑ ከእርሱ ጋር በጸሎት መገናኘት ወይም ቢያንስ ለመገናኘት መሞከር ትልቅ ነገር እንደሆነ እና ሰዋዊ እና መንፈሳዊ ገጽታ መዋሄዱ በእውነት ልብን የሚነካ ነበር ብለዋል። “በየምዕራፎቹ የአስተንትኖ ጸሎቶችን ከሚያቀርቡት ጋር ከ200-300 የሚደርሱ በእንባ የሚያለቅሱ ምዕመናንን የሚያሳትፍ የመስቀል መንገድ ምስክርነት ብርቅ እንደሆነ ተናግረው፥ እነዚህ የጦርነት እንባዎች ከኢየሱስ እንባ ጋር የተጣመሩ መሆናቸውን ሊቀ ጳጳስ አቡነ ቪስቫልዳስ አስረድተዋል። የጋራ ጸሎታቸው ዋና ዓላማም በአገሪቱ ውስጥ ሰላም እንዲወርድ፣ እስረኞች ሁሉ እንዲፈቱ እና በሐዘን ውስጥ ለሚገኙት ቤተሰቦቻቸው መጽናናትን ለማግኘት እንደሆነ አስረድተዋል።

ብዙ መከራ የደረሰባቸው ሰዎች የኢየሱስ ክርስቶስን መከራ መካፈላቸው፣ የአንድን ሰው ተሞክሮ በእምነት መካፈል እና ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ማልቀስ እንደሆነ የገለጹት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ቪስቫልዳስ፥ የግል ተሞክሮ ቢያንስ በከፊል የኢየሱስ ክርስቶስን ሕማማት ለመረዳት እንደሚረዳ ማመናቸውን ተናግረው፥ ይህን የሚደግፉ ብዙ ሚስጢራት እና የሕሙማን ምስክርነቶች መኖራቸውን በመግለጽ ከዚያ በዘለለ እምነት በሚሰጠን ብርታት ስንሰቃይ በሕይወት ስንኖር ጸጋ እንደሚሆን አስረድተዋል።

ሌላው ገጽታ በዚያ ቅጽበት ሌላ ሰው እንዲያግዘን ወይም ሕመማችንን እንዲያውቅልን የማያስፈልግ መሆኑን የተናገሩት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ቪስቫልዳስ፥ ምክንያቱም መስቀልን በተጨባጭ እየኖሩት እና አብሮን ስላለ፣ በዚያ ወቅትም ከእግዚአብሔር ስለሆንን ይህ የእርሱ ጸጋ እንደሆነ አስረድተዋል።

እንደ ሁለቱም የቀን መቁጠሪያዎች ማለትም እንደ ግሪጎሮሳውያን እና ጁሊዮስ አቆጣጠር መሠረት የዘንድሮውን ብርሃነ ትንሳኤ ሁሉም አብያተ ክርስቲያናት የሕማማት ሳምንትን እና የትንሳኤ በዓልን በተመሳሳይ ቀን እንደሚያከብሩ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ቪስቫልዳስ ገልጸው፥ ይህም ደስታን እንዳጎናጸፋቸው እና እንደዚሁም በብዙ የካቶሊክ፣ የኦርቶዶክስ እና የፕሮቴስታንት ወንድሞች ዘንድ የደስታ ስሜት እንደፈጠረ ማየታቸውን ገልጸዋል።

ብርሃነ ትንሳኤውን በኅበረት ማክበር ደስታን እንደሚሰጥ የተናገሩት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ቪስቫልዳስ፥ በእውነቱ በመስቀል መንገድ ጸሎት ወቅት የጦር እስረኞች እንዲፈቱ እና በዩክሬን ሰላም እንዲወርድ ከመለመን በተጨማሪ፣ ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጤንነት መጸለያቸውን፣ አብያተ ክርስቲያናት ከሌሎች ማኅበረሰቦች ጋር ሆነው የብርሃነ ትንሳኤውን በዓል በአንድነት ለማክበር የሚያስችላቸውን ጸጋ እግዚአብሔር እንዲሰጣቸው መጸለያቸውን ተናግረዋል።

 

15 Apr 2025, 17:19