ፈልግ

የዩን ተቃዋሚዎች መጋቢት 27 ቀን 2017 ዓ.ም. በሴኡል በሚገኘው የጊዮንግቦክጉንግ ቤተ መንግስት ፊት ለፊት ያካሄዱት የተቃውሞ ሰልፍ ላይ ባንዲራዎችን ሲያውለበልቡ የዩን ተቃዋሚዎች መጋቢት 27 ቀን 2017 ዓ.ም. በሴኡል በሚገኘው የጊዮንግቦክጉንግ ቤተ መንግስት ፊት ለፊት ያካሄዱት የተቃውሞ ሰልፍ ላይ ባንዲራዎችን ሲያውለበልቡ  (AFP or licensors)

የኮሪያ ብጹአን ጳጳሳት የፕሬዝዳንት ዩን ከስልጣን መወገድን ተከትሎ ህዝቡ አንድነቱን እንዲያጠናክር አሳሰቡ

የደቡብ ኮሪያ ፕሬዝዳንት ዩን ሱክ ዮል ከስልጣን መነሳታቸውን ተከትሎ ሃገሪቷ ለአዲስ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ እየተዘጋጀች ሲሆን፥ የሃገሪቷ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ብጹአን ጳጳሳት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በመጣው የፖለቲካ ጽንፈኝነት ምክንያት የብሄራዊ አንድነት እና እርቅ አስፈላጊነትን ገልጸዋል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

ህዳር ወር ላይ አገራቸው በወታደራዊ ዕዝ ስር እንድትሆን ያወጁት የደቡብ ኮሪያው ፕሬዚዳንት ዩን ሱክ ላይ ክስ ለመመሥረት ከአራት ወራት ሕጋዊ ሂደቶች እና የፖለቲካ ውዥንብር በኋላ በህገ-መንግስታዊ ፍርድ ቤት በማይለወጥ ውሳኔ መጋቢት 26 ከስልጣናቸው የተነሱ ሲሆን፥ በሃገሪቱ ታሪክ በ2009 ዓ.ም. ከስልጣን ከተባረሩት ከፓርክ ጊዩን ሂ በኋላ ሁለተኛው የደቡብ ኮሪያ ፕሬዝዳንት እንደሆኑ ተዘግቧል።

ፕረዚዳንት ዮን ህዳር 24 ቀን 2017 ዓ.ም. ወታደራዊ ህግ ወይም ማርሻል ሎው ለማወጅ ባደረጉት ያልተሳካ ሙከራ ምክንያት በቁጥጥር ስር እንዲውሉ የእስር ትዕዛዝ የወጣባቸው የመጀመሪያው የደቡብ ኮሪያ ፕሬዚደንት ሲሆኑ፥ ይህም በእስያ በአራተኛ ደረጃ ላይ የምትገኘው ባለትልቅ ኢኮኖሚዋ ደቡብ ኮርያ የውስጥ የፖለቲካ ትርምስን ቀስቅሷል።

የደቡብ ኮሪያ ፕሬዚዳንት ዲሞክራሲ በሰፈነባት አገራቸው በወታደራዊ ሕግ (ማርሻል ሎው) ስር እንድትሆን ማክሰኞ፣ ኅዳር 24 ቀን 2017 ዓ.ም. ማወጃቸው አገሪቱን ያስደነገጠ ክስተት ነበር።

ነገር ግን ወታደራዊ ሕጉ በታወጀ ሁለት ሰዓት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ የፓርላማ አባላቱ ፕሬዚዳንቱን ተቃውመው በምክር ቤት ከተሰበሰቡ በኋላ አስቸኳይ ድምጽ በመስጠት ውሳኔውን አግደዋል።

ፕረዚዳንት ዩን የሰሜን ኮሪያ ደጋፊ ኃይሎችን ለማጥፋት እና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ለማስከበር የወሰኑት የወታደራዊ ህግ ወይም ማርሻል ሎው ውሳኔን አስፈላጊ እርምጃ አድርገው ቢያቀርቡም፥ በተቃዋሚዎቻቸው ዘንድ ከፍተኛ ተቃውሞ አስከትሎ ውሳኔው በፍጥነት ሊቀለበስ ችሏል።

ከዚህም ባለፈ ፕሬዚዳንቱ አገሪቱ በአምስት አስርት ዓመታት አይታው የማታውቀውን ይህንን አስደንጋጭ ውሳኔ ለመወሰን ምክንያታቸው “ፀረ መንግሥት ኃይሎች” እና የሰሜን ኮሪያን ስጋት እንደሆነ ጠቅሰው ነበር።

ወታደራዊ ሕግ (ማርሻል ሎው) የሲቪል ባለሥልጣናት ሥራቸውን በአግባቡ ማከናወን እንደማይችሉ በሚቆጠርበት ጊዜ ወታደራዊ ባለሥልጣናት እንዲመሩ የሚደረግበት ጊዜያዊ አገዛዝ እንደሆነ ይታወቃል።

አንዲት አገር በወታደራዊ ሕግ ስር በምትሆንበት ወቅት የሲቪል መብቶች መታደግ እንዲሁም ወታደራዊ ሕጉ ሊራዘም የሚችልበት ሁኔታ ይፈጠራል።
በደቡብ ኮሪያ ለመጨረሻ ጊዜ ወታደራዊ ሕግ የታወጀው በአውሮፓውያኑ 1979 ሲሆን፣ ወቅቱም አገሪቱን ለበርካታ ዘመናት የገዙት አምባገነኑ ፖርከ ቹንግ ሂ በመፈንቅለ መንግሥት መገደላቸውን ተከትሎ ነው።

ከብዙ ውጣ ውረድ በኋላ ሁከትን በማስነሳት ተከሰው እስር ቤት የገቡት ዩን፥ በሴኡል የሚገኘው ፍርድ ቤት በቴክኒክ ሰበብ እስሩን በመሰረዙ የካቲት 28 ቀን 2017 ዓ.ም. ከእስር መፈታታቸው ይታወሳል።

አዲስ ምርጫ በ60 ቀናት ውስጥ ይካሄዳል
የመጨረሻውን ብይን ለመስጠት በህገ-መንግሥታዊ ፍርድ ቤት የተሰየሙት ስምንቱም ዳኞች ፕረዚዳንቱ ከሥራ የማገድ ውሳኔውን በሙሉ ድምፅ ያጸደቁ ሲሆን፥ በውሳኔያቸውም መሰረት የፕረዚዳንቱ ድርጊት መሰረታዊ የዴሞክራሲ መርሆዎችን የሚጥስ መሆኑን በተለይም የመከላከያ ኃይሎችን የፖለቲካ ገለልተኝነት የሚጻረር መሆኑን አፅንዖት ሰጥተዋል።

የፕረዚዳንት ዩን ከስልጣን መባረር ተከትሎ ደቡብ ኮሪያ በአሁኑ ወቅት በ60 ቀናት ውስጥ አዲስ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ለማካሄድ እየተዘጋጀች ሲሆን፥ በደቡብ ኮሪያ ማህበረሰብ ውስጥ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በመጣው የጽንፈኝነት ሂደት ውስጥ አንዳንዶች ዩንን በ"ፀረ-መንግስት" አካላት ላይ እንደ አስፈላጊ ኃይል አድርገው እንደሚመለከቷቸው እና ሌሎቹ ደግሞ ለዴሞክራሲያዊ መረጋጋት ጠንቅ አድርገው እንደሚገልጿቸው ዘገባዎች ያሳያሉ።

በደቡብ ኮሪያ ማህበረሰብ ውስጥ ያለው የፖለቲካ ጽንፈኝነት
በህብረተሰቡ መካከል የሚታየው ክፍፍል ለፍርዱ በተሰጠው ምላሽ የተንጸባረቀ ሲሆን፥ የተቃዋሚ ህግ አውጭዎች እና ፀረ-ዩን ተቃዋሚዎች የፍርድ ውሳኔውን በመቀበል ደስታቸውን እየገለጹ ሲሆን፥ የፕረዚዳንቱ ደጋፊዎች ደግሞ ውሳኔውን በመቃወም በቁጣ ምላሽ ሰጥተዋል።

ሀገሪቱ ለዚህ አዲስ ወሳኝ ምዕራፍ እየተዘጋጀች ባለችበት በአሁኑ ወቅት፥ የኮሪያ ብጹአን ጳጳሳት በድጋሚ የብሄራዊ አንድነት እና እርቅ አስፈላጊነትን አጽንዖት ሰጥተው ገልጸዋል።

አርብ ዕለት በተለቀቀው የብጹአን ጳጳሳቱ መግለጫ የስዎን ጳጳስ የሆኑት የደቡብ ኮሪያ ጳጳሳት ጉባኤ (KBCK) ፕሬዝዳንት ብጹእ አቡነ ማቲያስ ሪ ሎንግ-ሆን ኃላፊነት የሚሰማው እና ሥነ ምግባር ያለው መሪን መምረጥ ማህበራዊ ስምምነትን ወደነበረበት ለመመለስ ወሳኝ እንደሆነ በመጥቀስ፥ ፖለቲከኞች ከፓርቲያዊ ግጭቶች ይልቅ ለህዝቡ ደህንነት ቅድሚያ እንዲሰጡ አሳስበዋል።

“ፕሬዝዳንታዊ ሥልጣን ማለት በሕዝብ የተወከለ፣ ሕዝብን የሚያገለግል፣ የዜጎችን ሕይወትና ንብረት ለመጠበቅ በማንኛውም ጊዜ መስዋዕትነት የሚከፍል አመለካከትና ፍላጎት ያለው መሆኑን የተረዳ መሪ መምረጥ አለብን”

ብጹአን ጳጳሳት ምርጫው ሰላማዊ እንዲሆን ይጸልያሉ
ብጹአን ጳጳሳቱ ሁሉም የመንግስት አካላት “የህዝቡን አመኔታ መልሶ ለማግኘት እና መግባባት ላይ ለመድረስ የተቻለውን ሁሉ ጥረት እንዲያደርጉ” እና ፖለቲከኞች “ህዝብን ለማገልገል መመረጣቸውን እንዳይዘነጉ እንዲሁም በሰላም አብሮ ለመኖር እርስ በርስ የመከባበር እና የመደማመጥ ፖለቲካን እንዲያራምዱ ጥሪ አቅርበዋል።

ብጹእ አቡነ ሪ ሎንግ ሁን “ከማህበራዊ እርቅ እና የጋራ ጥቅም አንጻር ኃላፊነት የሚሰማው እና ሥነ ምግባር ያለው መሪን የመምረጥ ሂደት ዴሞክራሲያዊ እና ብስለት ባለው መንገድ መከናወን አለበት” በማለት የፃፉ ሲሆን፥ ብጹአን ጳጳሳቱ በበኩላቸው፣ “በኮሪያ የምትገኘው የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ቀጣዩ የሕዝብ ምርጫ በአገራችን ፍትሕና እውነተኛ ሰላም እንዲሰፍን የማዕዘን ድንጋይ እንዲሆን ከልቧ ትጸልያለች” ሲሉ ገልጸዋል።

“ዴሞክራሲ ሥርዓትን በማክበር ላይ የተመሰረተ ነው”
‘ፊደስ ኤጀንሲ’ የተሰኘው የካቶሊክ ሚዲያ እንደዘገበው ይህ መግለጫ ከፍርዱ በፊት ውጥረቱ እየጨመረ በመምጣቱ በደቡብ ኮሪያ የሃይማኖት መሪዎች ከተጀመሩት ተከታታይ የሰላም ጥሪዎች መካከል የመጨረሻው መሆኑን ገልጿል።

የካቲት 26 በደቡብ ኮሪያ የምትገኘው የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያንን ጨምሮ የዋና ዋና ሃይማኖቶች ማኅበር “የሕዝብ መግለጫ” በሚል ርዕስ ባወጡት የጋራ መግለጫ ቀውሱ በተረጋጋ ሁኔታ እንዲፈታ የሃገሪቱ ዜጎች የሕገ መንግሥቱ ፍርድ ቤት የሰጠውን ውሳኔ እንዲያከብሩ እና እንዲቀበሉት በማሳሰብ፥ “ዲሞክራሲ የተመሠረተው ሕግን በማክበር ላይ ነው” ሲሉ የሃይማኖት መሪዎቹ ጽፈው እንደነበር ይታወሳል።

የቅድስት መንበር የካህናት ጽህፈት ቤት ሃላፊ የሆኑት ኮሪያዊው ብፁዕ ካርዲናል ላዛሮ ዩ ሄንግ-ሲክ መጋቢት 12 በኮሪያ ለሚገኙ የካቶሊክ ምእመናን ባስተላለፉት መልዕክት “የፍትሕ እና የኅሊናን ድምፅ” እንዲሰሙ ጥሪ አቅርበዋል።

ፍርዱ ከመተላለፉ ጥቂት ቀደም ብሎ መጋቢት 23፣ የኮሪያ ብጹአን ጳጳሳት ጉባኤ ሁሉም ዜጎች ውሳኔውን እንዲቀበሉ እና እንዲያከብሩ ተስፋ በማድረግ በኮሪያ የምትገኘው ካቶሊካዊት ቤተክርስትያን እንደምትጸልይ በመግለጽ፥ “በዚህ መንገድ ሀገራችን ጠንካራ ዴሞክራሲያዊት ሀገር ለመሆን ተጨማሪ እርምጃ ትወስዳለች” ብለዋል።
 

07 Apr 2025, 15:25