ፈልግ

የሕሙማን እና የጤና ባለሞያዎች ኢዮቤልዩ የሕሙማን እና የጤና ባለሞያዎች ኢዮቤልዩ   (Vatican Media)

በጤና እንክብካቤ እና በሥነ-ምግባር ውስጥ ተጋላጭነትን ማካተት እንደሚገባ ተነገረ

የሕሙማን እና የጤና ባለሞያዎች ኢዮቤልዩ በዓልን ምክንያት በማድረግ በካቶሊካዊ የምርምር እና ጥናት ዩኒቨርስቲዎች አንድነት የተዘጋጀው ሴሚናር በሰው ልጅ አቅመ ደካማነት ላይ ባለው የሥነ-ምግባር እና የማኅበረሰባዊነት ገጽታ ላይ ተወያይቷል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

“ተጋላጭነት ውስንነት ሳይሆን ነገር ግን አንድ የሚያደርገን እና ወደ ኃላፊነት የሚጠራን ጥንካሬ ነው” የሚለውን መልዕክት፥ ካቶሊካዊ የምርምር እና ጥናት ዩኒቨርስቲዎች አንድነት ያዘጋጀው ጥናታዊ ሴሚናር ዋና ርዕሥ እንደሆነ ተመልክቷል።

ሮም ሰኞ መጋቢት 29/2017 ዓ. ም. የተካሄደውን ሴሚናር በጋራ ያዘጋጁት በአውስትራሊያ የሚገኝ ካቶሊክ ዩኒቨርሲቲ እና የሕሙማን እና የጤና ባለሞያዎች ኢዮቤልዩ አስተባባሪ ጽሕፈት ቤት ሲሆኑ በዚህ ሴሚናር ላይ ከዓለም ዙሪያ የመጡ ወጣት ምሁራን ተሳታፊ ሆነዋል።

ሴሚናሩ የተካሄደው ሥነ-ምግባራዊን እና የተጋላጭነትን ማኅበራዊ ገጽታዎችን ለመተንተን እና ተቋማትም አቅመ ደካማነትን እንደ ድክመት ሳይሆን ነገር ግን እንደ የሰው ልጅ ልምድ እና የትክክለኛ እንክብካቤ ዋና አካል አድርገው እንዲገነዘቡ ለማሳሰብ እንደሆነ ታውቋል።

ውይይቱ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ 2024 ዓ. ም. የተጀመረ የጥናት ሥራ ፍጻሜ ሲሆን፥ በአውስትራሊያ የሚገኝ ካቶሊክ ዩኒቨርሲቲ በዘረጋው ዓለም አቀፍ አውታረመረብ በኩል የዶክትሬት ተማሪዎችን በማሰባሰብ የእርስ በርስ ትምህርታዊ ምርምሮቻቸውን እንዲለዋወጡ አድርጓል። ውይይቱ የተካሄደው ተጋላጭነትን የመለወጥ አቅም ካለው የጄኔቲክ ሙከራ እስከ ዕለተ ሞት ድረስ የሚደረግ እንክብካቤን፣ በግጭት ቀጣናዎች ከሚቀርቡ የአብያተ ክርስቲያን የጤና አጠባበቅ ሥነ-ምግባር በጎነት እና ፍትህ ድረስ ያሉ ፍልስፍናዊ ጥናቶችን በአንድ የጋራ ጭብጥ ላይ በመሰብሰብ እንደሆነ ተመልክቷል።

የተጋላጭነትን ጽንሰ-ሃሳብ እንደገና ማቅረብ

በውይይቱ መግቢያ ላይ የኩዊንስላንድ ባዮኤቲክስ ማዕከል ዳይሬክተር እና በአውስትራሊያ የሚገኝ ካቶሊክ ዩኒቨርሲቲ የሥራ ቡድን ሊቀ መንበር የሆኑት ዴቪድ ኪርችሆፈር፥ ከወረርሽኙ በኋላ ያለውን ፅንሰ-ሃሳብ ማስተካከል አስፈላጊነት ላይ በማትኮር ንግግር አድርገዋል።

ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ እና ከሥራ ቡድኑ መቋቋም በኋላ በካቶሊክ ዩኒቨርሲቲዎች በተደረጉ የምርምር ማዕቀፍ ውስጥ ተጋላጭነት የሃሳብ ማዕከል መሆኑን መገንዘባቸውን እና ይህም በተማሪዎች መካከል ያለው ትብብር ቁርጠኝነት ተጨባጭ መግለጫ መሆኑን ዳይሬክተሩ አስረድተዋል።

በሴሚናሩ ላይ በቅድስት መንበር የአውስትራሊያ አምባሳደር ኬይት ፒት ከተቋማት መሪዎች እና የጤና አጠባበቅ ባለሙያዎች ጋር ተገኝተዋል።

የአውስትራሊያ ካቶሊክ ዩኒቨርሲቲ ቻንስለር እና “ሜርሲ ሔልዝ አውስትራሊያ” የተሰኘ ድርጅት የቦርድ ሰብሳቢ ቨርጂኒያ ቡርኬ፥ ዛሬ ተበታትኖ በሚገኝ የቁጥጥር መልክዓ ምድር በተለይም በጤና አጠባበቅ እና በአረጋውያን እንክብካቤ ዘርፎች የሥነ-ምግባር ግልፅነት አስፈላጊነትን አጉልተዋል።

ካቶሊካዊ የምርምር እና የጥናት ዩኒቨርስቲዎች ኅብረት ተነሳሽነት ለጤና አጠባበቅ ዘርፉ ተጨማሪ እሴት ሊሰጥ የሚችል እና ወጥ የሆነ የሥነ-ምግባር ማዕቀፍ በማበርከት የጋራ አቅጣጫን ይሰጣል” ሲሉ አስረድተዋል።

ለጋራ ዕድገት የሚሆን ቦታ

በክብ ጠረጴዛው ዙሪያ የተካሄደው ውይይት ከሰባት ሀገራት የተውጣጡ ድምጾችን እና የተለያዩ የጥናት ዘርፎችን ያሰባሰበ ሲሆን፥ የከፍተኛ ተቋም ተማሪዎች በተጋላጭነት ላይ ባለ የጋራ እንክብካቤ እይታ በመመራት በየመስካቸው የተወሰዱ ግንዛቤዎችን አካፍለዋል።

የፖርቱጋል ካቶሊካ ዩኒቨርሲቲ ተወካይ ጆአና ራሞስ በበኩላቸው፥ “ተጋላጭነት በብዙዎች ዘንድ እንደ ግል ጉዳይ የሚታይ መሆኑን ገልጸው፥ ነገር ግን በውይይታቸው መካከል እንደ አንድ የጋራ ጉዳይ ተደርጎ መቅረቡን አስረድተዋል። በተጨማሪም ሥነ-ምግባር፣ ሳይንስ እና ሰብዓዊ ክብር እርስ በርስ የሚገናኙበት ቦታ አድርገው ማየት መጀመራቸውን ተናግረዋል።

በቅዱስ ልበ ኢየሱስ ካቶሊክ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ፕሮፌሰር እና የቡድኑ አባል የሆኑት ሲሞን ቤሬታ በበኩላቸው፥ በዚህ እንደገና በቀረበው ጽንሰ-ሃሳብ ላይ በተሰጠው ሥነ-መለኮታዊ እና ሕዝባዊ ድምጽ አጽንኦት ሰጥተው፥ “ተማሪዎቹ ተጋላጭነትን እንደ ደካማነት ብቻ ሳይሆን ለሌሎችም እንደ ሃላፊነት የሚሰጥ እንደሆነ መመልከታቸውን ገልጸው፥ ይህም ጥሩ አብሮ የመኖር መርህ እና “ሁላችንም ወንድማማቾች ነን” የሚለው የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሐዋርያዊ ቃለ-ምዕዳን እና የደጉ ሳምራዊ መርህ እንደሆነ አስረድተዋል።

በውይይቱ ማጠቃለያ፥ የነገረ መለኮት ምሁር እና በቦስተን ኮሌጅ የግሎባል ተሳትፎ ምክትል ሃላፊ አባ ጄምስ ኪናን በተጋላጭነት ላይ ጥልቅ አስተንትኖ በማድረግ ሥነ-ምግባራዊ ገለጻ አቅርበዋል።

አባ ጄምስ በገለጻቸው፥ “ተጋላጭነት ለጤና አጠባበቅ ሥነ-ምግባር ጠንካራ ጽንሰ-ሃሳብ ነው” ብለው፥ ነገር ግን በምላሽ ሰጪዎች እንደሚወሰን አስረድተው፥ ነርሶች፣ ሐኪሞች፣ የተለያዩ እንክብካቤ ሰጪዎች እራሳቸውን እንደ ተጋላጭ አድርገው ማየት እንዳለባቸው ተናግረው፥ “ይህም በጊዜያችን ለተጋላጭነት ኃይል የሚሰጥ መሠረታዊ ግልጽነት ነው” ሲሉ አስረድተዋል።

ካቶሊካዊ የምርምር እና የጥናት ዩኒቨርስቲዎች ኅብረት ዋና ጸሃፊ ፒየር ሳንድሮ ኮኮንቼሊም ይህንን መንፈስ በማስተጋባት፥ ኅብረቱ በምሁራን ትብብር ውይይትን እና ሥነ-ምግባርን የተላበሰ አመራር ለማጎልበት ያለውን ቁርጠኝነት አረጋግጠዋል።

“ጥልቅ በሆኑ ልዩነቶች እና አለመተማመን በሚታይበት የሳይንስ ዓለም አቀፍ አውድ ውስጥ የተካሄደው ገንቢ ውይይት፣ የምሁራኑ ጥናት የሰውን ልጅ ክብር ዋና ማዕከል በማድረግ ለጋራ ጥቅም ተጨባጭ አስተዋፅዖ ማበርከቱን ያሳያል” ብለዋል።

 

09 Apr 2025, 15:18