የኡጋንዳ ብጹአን ጳጳሳት ‘ሀገር አደጋ ላይ ነች’ ሲሉ አስጠነቀቁ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
የኡጋንዳ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ብጹአን ጳጳሳት ሀገሪቱ እየተስፋፋ የመጣውን ፖለቲካ እና ማህበራዊ አለመረጋጋት እንድትጋፈጥ ጥሪ ያቀረቡ ሲሆን፥ ሀገሪቱ በአሁኑ ወቅት “ጫፍ ላይ እንደምትገኝ” ጠቅሰው፥ ወደ ፍትህ፣ ውይይት እና የሥነ ምግባር እሴቶች በአስቸኳይ እንድትመለስ አሳስበዋል።
ግንቦት 26 ከሚከበረው የኡጋንዳ የሰማዕታት ቀን ቀደም ብሎ በወጣው ባለ 15 ገጽ የሃዋሪያዊ ደብዳቤ ላይ ብጹአን ጳጳሳቱ በሃገሪቷ ውስጥ ስቃይ፣ ሙስና፣ ስልጣንን አላግባብ መጠቀም እና ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣውን ኢፍትሃዊነትን “የዘመናችን አሳዛኝ እውነታዎች” በማለት ከገለጹ በኋላ፥ በእነዚህ ሁኔታዎች ከፍተኛ ስጋት እንዳደረባቸው አመላክተዋል።
የኡጋንዳ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ብጹአን ጳጳሳት ጉባኤ ሊቀ መንበር ብጹእ አቡነ ጆሴፍ አንቶኒ ሃገሪቱ ላይ እየታየ ባለው ነገር ስጋታቸውን ሲገልጹ፥ “ኡጋንዳ የአደጋ ጫፍ ላይ ነች፥ የአቅጣጫ ለውጥ በአስቸኳይ ያስፈልጋል” ካሉ በኋላ፥ በሃገሪቷ ታሪክ ወሳኝ ወቅት ላይ መሆናቸውን ጠቅሰው፥ “አሁኑኑ እርምጃ ካልወሰድን ወደማንወጣው ትርምስ ልንገባ እንችላለን” በማለት አሳስበዋል።
ጳጳሳቱ በደብዳቤው ላይ ለብሔራዊ መረጋጋት ስጋት ናቸው ያሉትን በመጥቀስ፥ ጎሰኝነት፣ የድህነት መስፋፋት፣ የወጣቶች ሥራ አጥነት እና በመንግስት ተቋማት ውስጥ ግልጽነት እና ተጠያቂነት አለመኖርን ጨምሮ የተለያዩ ስጋቶችን የገለጹ ሲሆን፥ የፖለቲካ መሪዎች በምንም መንገድ ስልጣን ለማግኘት የሚደረገውን ሩጫ በመተው በምትኩ የጋራ ጥቅምን በማስከበር ላይ እንዲያተኩሩ አሳስበዋል።
ብጹአን ጳጳሳቱ የማርቲን ሉተር ኪንግ ጁኒየር ቃላትን በመጥቀስ “በየትኛውም ቦታ የሚፈጸም ኢፍትሃዊነት በሁሉም ቦታ ለፍትህ ጠንቅ ነው” በማለት ጽፈዋል።
ሁከት እና ማሰቃየትን አውግዘዋል
ከዚህም በተጨማሪ ደብዳቤው በተለይ በ 2018 ዓ.ም. ከሚካሄደው አገራዊ ምርጫ በፊት፣ በተለይ እየታየ ባለው የፖለቲካ ፉክክር ውስጥ እየጨመረ የመጣውን የሁከት እና የማሰቃየት ድርጊቶችን ያስጠነቀቀ ሲሆን፥ የካምፓላው ሊቀ ጳጳስ ብጹእ አቡነ ፖል ሴሞገሬሬ በፖለቲካው መድረክ ላይ እየታየ ያለውን እና “ጭካኔ እና ስድብ” ሲሉ የገለጹትን ተግባር አውግዘዋል።
ብጹእነታቸው የካሳና ሉዌሮ ሀገረ ስብከት 28ኛ ዓመት የምስረታ በዓል ላይ ባደረጉት ንግግር በቅርቡ በሰሜናዊ ካዌምፔ በነበረው መርሃ ግብር ወቅት የተከሰተው ነገር የፖለቲካ ስህተት ብቻ ሳይሆን የማስጠንቀቂያ ምልክት እንደሆነ በመጥቀስ፥ “የማሰቃየት፣ የማስፈራራት እና የማጎሳቆል ተግባራትን እያየን እንዳላየ መሆን አንችልም” ብለዋል።
ሊቀ ጳጳሱ በኡጋንዳ የተከሰተውን ያለፈውን ችግር በተለይም እንደ ታላቋ ሉዌሮ ባሉ ክልሎች እየተከሰተ ያለውን ስቃይ መሪዎችን እና ዜጎችን በማስታወስ፥ “በዚች ምድር ላይ የፈሰሰውን ደም አንርሳ፣ ግፍ እና ብጥብጥ ዳግም ስር ሰዶ ሊቆም አይገባም” በማለት ነዋሪዎቿ በማንኛውም መልኩ ፖለቲካዊ ጥቃትን እንዳይቀበሉ ጥሪ አቅርበዋል።
ለጋዜጠኞች እና ህግ አውጪዎች የቀረበ ጥሪ
ጳጳሳቱ ለመገናኛ ብዙኃን ባቀረቡት ቀጥተኛ ጥሪ፣ ጋዜጠኞች የሰላምና የተጠያቂነት መልዕክቶችን እንዲያበረታቱ ያሳሰቡ ሲሆን፥ ሊቀ ጳጳስ ሴሞገረሬ ፕሬስ ህዝባዊ ንግግርን በመቅረጽ በኩል ያለውን ጠቀሜታ አበክረው በመግለጽ፥ “ሚዲያ ውጥረቶችን ለማቀጣጠል ጥቅም ላይ መዋል የለበትም፥ ነገር ግን መግባባትን እና የዜጎችን ኃላፊነት የተሞላበት ተሳትፎ ማበረታታት አለበት” ብለዋል።
ቤተክርስቲያኒቷ ፓርላማው ፍትሃዊ በሆነ መንገድ ህግ እንዲያወጣ የጠየቀች ሲሆን፥ በተለይም በወታደራዊ ፍርድ ቤት የሚዳኙ ሰላማዊ ዜጎችን ጉዳይ በማንሳት ሊቀ ጳጳስ ሴሞገረሬ “የእኛ ሕግ አውጪዎች የጋራ ጥቅምን፣ ፍትህን እና ለሁሉም ሰው ነፃነትን የሚያበረታቱ ሕጎች እንዲያወጡ እንጸልያለን” በማለት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
የቤተክርስቲያን ሚና እና ሞራላዊ ሃላፊነት
የኡጋንዳ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ብጹአን ጳጳሳት ጉባኤ ሊቀ መንበር ብጹእ አቡነ ጆሴፍ አንቶኒ ዚዋ አጽንኦት ሰጥተው እንደተናገሩት ቤተክርስቲያኒቷ በምንም ዓይነት ሁኔታ ወገንተኛ እንዳልሆነች፥ ነገር ግን ግፍ ሲፈጸም ዝም ማለት እንደማትችል ከገለጹ በኋላ፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ “የጋራ ጥቅምን የሚሻ ፖለቲካ” ሲሉ ያቀረቡትን ጥሪ በመጥቀስ “በሁሉም የሰው ሕይወት ዘርፎች የሞራል ፍርድ መስጠት የቤተ ክርስቲያን ተልዕኮ አካል ነው” ብለዋል።
ደብዳቤው ከመጽሃፍ ቅዱስ ክፍል በዮሐንስ ወንጌል ላይ ያለውን አስተምህሮ መነሻ በማድረግ “እውነት አርነት ያወጣችኋል” በማለት አጥብቆ የገለጸ ሲሆን፥ ብጹአን ጳጳሳቱ ሁሉም ዩጋንዳውያን ምንም አይነት የፖለቲካ ወገንተኝነት ሳይኖራቸው እውነትን፣ ታማኝነትን እና ብሄራዊ ውይይትን እንዲቀበሉ ጥሪ አቅርበዋል።
ደብዳቤው በመጨረሻም ከፍርሃትና ከማታለል ፖለቲካ መራቅ እንደሚገባ በማሳሰብ፥ “ኡጋንዳ የሁላችንም ሃገር ነች፥ የዚህች ሀገር የወደፊት እጣ ፈንታ ዛሬ በምንመርጠው ምርጫ ላይ የተመሰረተ ነው” በማለት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።