የቀጣዩን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ምርጫ ዝግጅት የቀጣዩን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ምርጫ ዝግጅት  

ቀጣዩን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት መምረጥ የሚችሉ ካርዲናሎች እነማን እንደሚሆኑ ታወቀ

ግንቦት 29/2017 ዓ. ም. የሚካሄደው “ኮንክላቭ” የብጹዓን ካርዲናሎች ዝግ ጉባኤ መክፈቻ ሥነ-ሥርዓት ከመቼውም ጊዜ በላይ በቁጥር አነስተኛ የአውሮፓ አገራት ካርዲናሎት የሚሳተፉበት ይሆናል። ከሦስት አራተኛ በላይ የሚሆኑት 135 መራጭ ካርዲናሎች፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የካርዲናሎች ጉባኤን በማደስ የቤተ ክርስቲያኒቱን ልዩ ልዩ የሩቅ አከባቢዎችን የበለጠ በስፋት በማገናዘብ የሾሟቸው ናቸው።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በጠቅላላ የካርዲናሎች ጉባኤ ውስጥ የሚገኙት 135 መራጭ ካርዲናሎች በአምስቱ አህጉራት ውስጥ ከሚገኙ 71 የተለያዩ ሀገራት የተውጣጡ ናቸው። ከሦስት አራተኛ በላይ የሚሆኑት 108 ካርዲናሎች የተሾሙት በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሲሆን 22ቱ በቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቤኔዲክቶስ 16ኛ የተሾሙ እና አምስቱ በቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ 2ኛ የተሾሙ ሲሆኑ ይህም የ “ኮንክላቭ” ወይም የዝግ ጉባኤ አንጋፋ ካርዲናሎች ያደርጋቸዋል። እነርሱም ፈረንሳዊው ካርዲናል ፊሊፕ ባርባሪን፣ ክሮኤሺያዊው ካርዲናል ጆሲፕ ቦዛኒች፣ ከቦስኒያ እና ሄርዞጎቪና ካርዲናል ቪንኮ ፑልጂች እና ከጋና ካርዲናል ፒተር ቱርክሰን ናቸው።


ከአውሮፓ የመጡ አነስተኛ የዝግ ጉባኤ ተካፋዮች

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በ12 ዓመታት የርዕሠ ሊቃነ ጳጳስነት ዘመናቸው የካርዲናሎች ጉባኤን በከፍተኛ ደረጃ በማደስ አውሮፓ ላይ ትኩረት ከመስጠውት ይልቅ ይበልጥ ዓለም አቀፋዊ ይዘት እንዲኖረው አድርገውታል። ይህ የሁለቱንም ሟቹ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ግላዊ የካቶሊካዊነት ዝንባሌን ወደ ደቡቡ ዓለም በማዞር እና በሩቁ የዓለማችን ክፍሎች ላይ በማትኮር የወደፊቱ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ከጊዜ ወደ ጊዜ አውሮፓዊ ያልሆነ ገጽታ ሊኖራት እንደሚችል የሚያሳይ ነው።

በዝግ ጉባኤው ለመጀመሪያ ጊዜ 12 አገራት በአገራቸው ተወላጅ መራጭ ካርዲናሎች ይወከላሉ። ከእነዚህ አገራት መጥተው ዝግ ጉባኤውን የሚካፈሉት፥ ካርዲናል ቺቢሊ ላንግሎይስ ከሄይቲ፣ ካርዲናል አርሊንዶ ፉርታዶ ጎሜዝ ከኬፕ ቨርዴ፣ ካርዲናል ዴዎዶኔ ንዛፓላይንጋ ከመካከለኛው አፍሪካ ሪፐብሊክ፣ ካርዲናል ጆን ሪባት ከፓፑዋ ኒው ጊኒ፣ ካርዲናል ሴባስቲያን ፍራንሲስ ከማሌዥያ፣ ካርዲናል አንድሬስ አርቦሬሉስ ከስዊድን፤ ካርዲናል ዣን ክላውድ ሆሌሪች ከሉክሰምበርግ፣ ካርዲናል ቪርጂሊዮ ዶ ካርሞ ዳ ሲልቫ ከቲሞር ሌስቴ፣ ካርዲናል ዊልያም ሴንግ ቺ ጎህ ከሲንጋፖር፣ ካርዲናል አዳልቤርቶ ማርቲኔዝ ፍሎሬስ ከፓራጓይ፣ ካርዲናል ስቴፈን አሜዩ ማርቲን ሙላ ከደቡብ ሱዳን፣ እና ካርዲናል ላዲስላቭ ኔሜት ከሰርቢያ ናቸው።

53 የአውሮፓ ካርዲናሎች

ይሁን እንጂ አውሮፓ አሁንም በጠቅላላ የካዲናሎች ጉባኤ ውስጥ ትልቅ ቁጥር ያለው ሲሆን፥ የቀድሞው የአውሮፓ አገራት ክልል 53 መራጭ ካርዲናሎች ያሉት እና ከእነዚህም መካከል አንዳንዶቹ ከአህጉሪቱ ውጭ በውጭ አገራት የሚገኙ ሀገረ ስብከቶችን የሚመሩ ወይም የቅድስት መንበር ሐዋርያዊ እንደራሴ ሆነው የሚያገለግሉ ናቸው። ጣሊያን 19 ካርዲናሎች፣ ፈረንሳይ 6 ካርዲናሎች እና ስፔን 5 ካርዲናሎች እንዳሏቸው ታውቋል።

37 ካርዲናሎች ከአሜሪካ፣ 23 ከእስያ፣ 18 ከአፍሪካ እና 4 ከኦሽንያ

አሜሪካ እና ላቲን አሜሪካ በድምሩ 37 መራጭ ካርዲናሎች ሲኖራቸው 16 ከሰሜን አሜሪካ፣ 4 ከመካከለኛው አሜሪካ እና 17 ከደቡብ አሜሪካ ናቸው። 23 ከኤዥያ፣ 18 ከአፍሪካ እና 4 ከኦሽንያ ናቸው።

የአውሮፓ ካርዲናሎች አሁንም በ “ኮንክላቭ” ወይም በዝግ ጉባኤ ውስጥ አብዛኞቹን ቁጥር የሚወክሉ ቢሆንም የተቀረው የዓለም ክፍል በግልጽ አውሮፓን በመብለጥ አሁንም የአሜሪካ፣ የመካከለኛው አሜሪካ እና የላቲን አሜሪካ መራጭ ካርዲናሎች ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ መጨመሩ ተመልክቷል።

ምንም እንኳን ክልላዊ ውክልና ብቻውን የአዲሱን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ምርጫ ውጤትን መወሰን ባይችልም በሌሎች ወሳኝ ሁኔታዎች ላይ ተጽእኖ ሊያሳድር ስለሚችል የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሚና ዓለም አቀፋዊ ተፅእኖን ከግምት ውስጥ በማስገባት ጂኦግራፊያዊ ገጽታው በቀላል ሊታለፍ አይችልም።

የመራጭ ካርዲናሎች ዕድሜን በተመለከተ

የመራጭ ካርዲናሎች ዕድሜን በተመለከተ በጠቅላላ የካርዲናሎች ጉባኤ ውስጥ ዝቅተኛ ዕድሜ ያላቸው በአውስትራሊያ የሚኖሩ ዩክሬናዊ ተወላጅ ካርዲናል ሚኮላ ባይቾክ ሲሆኑ ዕድሜያቸው 45 ዓመት ሲሆን በዕድሜ አንጋፋው ስፔናዊው ካርዲናል ካርሎስ ኦሶሮ ሲየራ ሲሆኑ ዕድሜያቸውም 79 ዓመት እንደሆነ ተገልጿል።

ስድስት ካርዲናሎች በሰባዎቹ ውስጥ የተወለዱ ሲሆን፥ በመጪው ዓመት ኅዳር ወር ላይ ዕድሜያቸው 55 ዓመት የሚሞላቸው የሮም ሀገረ ስብከት ረዳት ጳጳስ ካርዲናል ባልዳዛር ሬይና ናቸው። እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ 1971 ዓ. ም. የተወለዱት ካናዳዊው ካርዲናል ፍራንክ ሊዮ፣ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ 1972 ዓ. ም. የተወለዱት የሊቱዌኒያ ተወላጅ እና በሮም የታላቋ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ባዚሊካ ተባባሪ ሊቀ ካህናት ካርዲናል ሮላንዳስ ማኪሪካስ ናቸው። እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ 1973 ዓ. ም. የተወለዱት እና በጳጳሳዊ ምክር ቤት የሐይማኖት ተቋማት የጋራ ውይይት አስተባባሪ ጽሕፈት ቤት አስተዳዳሪ ህንዳዊው ካርዲናል ጆርጅ ጃኮብ ኮቫካድ፣ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ 1973 ዓ. ም. የተወለዱት ፖርቹጋላዊው ካርዲናል አሜሪኮ ማኑኤል አልቬስ አጉያር እና እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ 1974 ዓ. ም. የተወለዱት እና በሞንጎሊያ የኡላንባታር ሐዋርያዊ አስተዳዳሪ ጣሊያናዊ ተወላጅ ካርዲናል ጆርጆ ማሬንጎ ዝግ ጉባኤውን ለመጀመሪያ ጊዜ እንደሚሳተፉት ታውቋል።

በሌሎች የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙት እና በአርባዎቹ የተወለዱ 50 ካርዲናሎች፣ በሃምሳዎቹ ውስጥ የተወለዱት 47 ካርዲናሎች እና በስልሳዎቹ ውስጥ የተወለዱትን 31 ካርዲናሎችን ያካትታል። በዝግ ጉባኤው ላይ በርክተው የሚገኙት በአርባዎቹ የተወለዱት ሲሆኑ ዕድሜያቸው ወደ 78 የሚጠጋ 13 ካርዲናሎች እንደሆኑ ታውቋል።

33 ካርዲናሎች የገዳማዊ ማኅበራት አባላት ናቸው

ከመራጭ ካርዲናሎች መካከል 33ቱ የ18 የተለያዩ ገዳማት አባላት ናቸው። ከእነዚህም መካከል ጉባኤውን በብዙ ቁጥር የሚካፈሉት አምስት የዶን ቦስኮ ሳሌዥያዊ ማኅበር አባላት ሲሆኑ እነርሱም ካርዲናል ቻርለስ ማውንግ ቦ፣ ካርዲናል ቨርጂሊዮ ዶ ካርሞ ዳ ሲልቫ፣ ካርዲናል አንጄል ፈርናንዴዝ አርቲሜ፣ ካርዲናል ክሪስቶባል ሎፔዝ ሮሜሮ እና ካርዲናል ዳንኤል ስቱርላ በርሀውት እንደሆኑ ታውቋል። አራቱ ፍራንችስካዊያን አባላት፥ ካርዲናል ሉዊስ ካብሬራ ሄሬራ፣ ካርዲናል ፒየርባቲስታ ፒዛባላ፣ ካርዲናል ሃይሜ ስፔንገር እና ካርዲናል ሊዮናርዶ እስታይነር ሲሆኑ አራት ኢየሱሳያን ካርዲናል ስቴፈን ቾ ሳው-ያን፣ ካርዲናል ሚካኤል ቼርኒ፣ ካርዲናል ዣን ክሎድ ሆሌሪች እና ካርዲናል አንገል ሮሲ ናቸው። ሦስቱ ኮንቬንቿል ፍራንሲስካውያን ካርዲናል ፍራንሷ-ሀቪየር ቡስቲሎ፣ ካርዲናል ማውሮ ጋምቤቲ እና ካርዲናል ዶሚኒክ ማቲዩ ናቸው።

የመራጭ ካርዲናሎችን ዝግ ጉባኤን የሚሳተፉት ሁለት ዶሚኒካዊ አባቶች፥ ካርዲናል ጢሞቲ ራድክሊፍ እና ካርዲናል ዣን ፖል ቬስኮ፣ ሁለት የቤዛዊያን ማኅበር አባላት ካርዲናል ማይኮላ ባይቾክ እና አባ ጆሴፍ ቶቢን፣ ሁለት የመለኮታዊ ቃል ሚስዮናውያን ማኅበር አባላት ካርዲናል ታርሲስዮ ኪኩቺ እና ካርዲናል ላዲስላቭ ኔሜት ሲሆኑ፥ እያንዳንዳቸው ከሌሎች ማኅበራት ከተወከሉት መካከል የቅዱስ አጎስጢኖስ ማኅበር አባል ካርዲናል ሮበርት ፕሪቮስት፣ የካፑቺን ፍራንችስካውያን ማኅበር አባል ካርዲናል ፍሪዶሊን አምቦንጎ ቤሱንጉ፣ ቄርሜሎሳዊ ማኅበር አባል ካርዲናል አንድሬስ አርቦሬሊዩስ፣ የአቡነ ብሩክ ገዳም አባል ካርዲናል ኦራኒ ዮዋዎ ቴምፐስታ፣ የክላሬሲያውያን ማኅበር አባል ካርዲናል ቪሴንቴ ቦካሊች ኢግሊች፣ የፒዮስ አሥረኛ ተቋም አባል ካርዲናል ጄራልድ ላክሮክስ፣ የላዛሪስት ማኅበር አባል ኢትዮጵያዊ ካርዲናል ብጹዕ አቡነ ብርሃነየሱስ ደምረው ሱራፌል፣ የኮንሶላታ ሚስዮናዊ ማኅበር አባል ካርዲናል ጆርጆ ማሬንጎ ሲሆኑ ሁለት የተቀሩት የቅዱስ ልበ ኢየሱስ ሚስዮናዊ ማኅበር አባል አባ ጆን ሪባት እና የቅዱስ ስካላብሪኒ ማኅበር አባል አባ ፋቢዮ ባጆ እና አባ ዴዎዶኔ ንዛፓልይንጋ ናቸው።

ድምጽ ለመስጠት ብቁ ከሆኑት 135 ካርዲናሎች መካከል ሁለቱ በጤና ምክንያት በዝግ ጉባኤው ላይ መገኘት እንደማይችሉ ያረጋገጡ ሲሆን ይህም ጠቅላላ ቁጥሩን ወደ 133 ዝቅ ማድረጉ ታውቋል።

 

30 Apr 2025, 17:28