ፈልግ

የአዲሱ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ምርጫ በመጭው ሚያዝያ 29 እንደሚጀምር ተገለጸ

በሮም የሚገኙት ብጹዓን ካርዲናሎች 267ኛውን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳትን የሚመርጡበት ዝግ ጉባኤ ሚያዝያ 29/2017 ዓ. ም. እንደሚጀምሩ አስታውቀዋል። ካርዲናሎቹ ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የቀብር ሥነ-ሥርዓት በኋላ ለዘጠኝ ቀናት በሚቆይ ጠቅላላ ስብሰባ፣ አስተንትኖ እና በየዕለቱ መስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ላይ እንደሚገኙ ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ብጹዓን ካርዲናሎቹ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ነፍስ በእግዚአብሔር ዘንድ ዘላለማዊ ዕረፍት ታገኝ ዘንድ ለዘጠኝ ቀናት ጸሎት ሲያቀርቡ ከቆዩ በኋላ ከሚያዝያ 29/2017 ዓ. ም. ጀምሮ አዲስ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳትን ለመምረጥ ዝግ ጉባኤ ለመጀመር መስማማታቸው ታውቋል።

በሮም የሚገኙት ካርዲናሎች ሰኞ ሚያዝያ 20/2017 ዓ. ም. ማለዳ ላይ በቫቲካን ባካሄዱት አምስተኛ ጠቅላላ ጉባኤያቸው ከተሰበሰቡት 180 ካርዲናሎች መካከል አዲስ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳትን ለመምረጥ የበቁ ከ 100 በላይ ካርዲናሎች እንደሚሆኑ ወስነዋል።

ስብሰባው የሚካሄደው በቫቲካን በሚገኝ የሲስቲን ጸሎት ቤት ውስጥ ሲሆን፥ በምርጫ ቀናት ጸሎት ቤቱ ለጎብኚዎች ዝግ ሆኖ እንደሚቆይ ታውቋል።

በዝግ ጉባኤ ወቅት ምን ምን ይከናወናል?

ከጉባኤው ቀደም ብሎ መራጭ ካርዲናሎች በኅብረት ሆነው የምርጫ መጀመሪያ መስዋዕተ ቅዳሴን የሚያሳርጉ ሲሆን፥ ከሰዓት በኋላ ዝግ ጉባኤን ለማካሄድ ወደ ሲስቲን ጸሎት ቤት እንደሚያመሩ የምርጫ መርሃ ግብር ያመለክታል።

ቀጥሎም እያንዳንዱ መራጭ ካርዲናል በ “Universi Dominici Gregis” ኡኒቨርሲ ዶሚኒቺ ግሬጂስ” ወይም “መላው የእግዚአብሔር መንጋ” በሚለው የቤተ ክርስቲያኒቱ ሐዋርያዊ ደንብ አንቀጽ 53 ላይ እንደተደነገገው ምርጫውን በታማኝነት ለማካሄድ ቃለ መሐላን ይፈጽማሉ።

በቃለ መሐላው መሠረት የተመረጠ ካርዲናል “Munus Petrinum” የቅዱስ ጴጥሮስን ሐዋርያዊ መንበር ወይም የኩላዊት ቤተ ክርስቲያን እረኝነትን በታማኝነት ለመፈጸም ቃል ይገባል። ከዚህም በተጨማሪ ካርዲናሎቹ ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ምርጫ ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ላይ ፍጹም ምስጢራዊነትን ለመጠበቅ እና በምርጫው ውስጥ ማንኛውንም የውጭ ጣልቃገብ ሙከራዎችን ከመደገፍ ለመቆጠብ ቃል ይገባሉ።

በዚህ ጊዜ ጳጳሳዊ የሥርዓተ አምልኮ አስተባባሪ አባት በተጨማሪ “የኮንክላቭ” ወይም የዝግ ጉባኤ አባል ያልሆኑ አባቶች “extra omnes” የሲስቲን ጸሎት ቤት እንዲለቁ ትዕዛዝ ያስተላልፋሉ። ከመራጭ ካርዲናሎች በተጨመሪ በጸሎት ቤቱ ውስጥ መቅረት የሚችሉት ሁለተኛውን አስተንትኖ ለመምራት የተሰየሙት አባት እና የሥርዓተ አምልኮው አስተባባሪ አባት ብቻ ናቸው።

የአስተንትኖው ዋና ዓላማ በመራጭ ካርዲናሎች ላይ ባለው ከፍተኛ ሃላፊነት ላይ ያተኮረ እና በእግዚአብሔር ፊት ለዓለም አቀፋዊት ቤተ ክርስቲያን ጥቅም ሲባል ምርጫውን በግልጽ በመተግበር አስፈላጊነት ላይ ያተኮረ ይሆናል።

አስተንትኖው አንዴ ከቀረበ በኋላ ሁለቱም ማለትም የሥርዓተ አምልኮ አስተባባሪ አባት እና አስተንትኖን ለመምራት የተሰየሙት አባት ከጸሎት ቤቱ ይወጣሉ።

ከዚያም በዝግ ጉባኤ ሥነ-ሥርዓቶች ወይም “Ordo Sacrorum Rituum Conclavis” ቅደም ተከተል መሠረት መራጭ ካርዲናሎች የሚደግሙትን ጸሎቶች የጉባኤው መሪ ካርዲናል ካዳምጡ በኋላ ካርዲናሎቹ በድምጽ አሰጣጥ ሂደት ለመቀጠል ዝግጁ መሆናቸውን፣ ደንቦችን እና ሂደቶችን በተመለከተ ማብራሪያ የሚያስፈልጋቸው ጉዳዮች ካሉ ይጠይቃሉ።

ሁሉም የምርጫ ሂደቶች የሚከናወኑት በቫቲካን ሐዋርያዊ ሕንጻ ውስጥ በሚገኝ በሲስቲን ጸሎት ቤት ብቻ ሲሆን፥ ምርጫው እስኪጠናቀቅ ድረስ ጸሎት ቤቱ ሙሉ በሙሉ ተዘግቶ ይቆያል።

በምርጫው ሂደት ወቅት መራጭ ካርዲናሎች እጅግ አስቸኳይ ካልሆነ ጉዳይ በስተቀር የስልክ ጥሪዎችን ጨምሮ የጽሑፍ መልዕክቶችን ወይም ደብዳቤዎችን ከመላላክ እና ከውይይት መቆጠብ አለባቸው።

ምንም ዓይነት መልዕክት መላክም ሆነ መቀበል፣ ጋዜጦችን ወይም መጽሔቶችን መቀበል፣ የሬዲዮ ወይም የቴሌቪዥን ስርጭቶችን መከታተል አይፈቀድላቸውም።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳትን ለመምረጥ ስንት ድምጽ ያስፈልጋል?

አዲስ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳትን በትክክል ለመምረጥ ከመራጮች ድምጽ መካከል ሁለት ሦስተኛ አብላጫ ድምጽ ያስፈልጋል።

የጠቅላላ መራጮች ቁጥር በሦስት እኩል ድምጽ የማይካፈል ከሆነ ተጨማሪ የድምጽ አሰጣጥ ሂደትን ማካሄድ አስፈላጊ ይሆናል።

ድምጽ መስጠት የሚጀመረው በመጀመሪያው ቀን ከሰዓት በኋላ ከሆነ ለአንድ ዙር ብቻ ሆኖ በቀጣዮቹ ቀናት ጠዋት እና ከሰዓት በኋላ በማድረግ ሁለት የምርጫ ሂደቶች ይካሄዳሉ።

የምርጫ ድምጾች ከተቆጠሩ በኋላ ሁሉም የድምፅ መስጫዎች ወረቀቶች እንዲቃጠሉ ይደረጋል። የድምጽ መስጫ ውጤቱ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት አለመመረጣቸውን የሚገልጽ ከሆነ በሲስቲን ጸሎት ቤት በኩል ጥቁር ጭስ እንዲወጣ ይደረጋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት የተመረጡ እንደሆነ ግን በጭስ መውጫው በኩል ነጭ ጭስ እንዲወጣ ይደረጋል።

መራጭ ካርዲናሎች ከሦስት ቀናት ያልተቋረጠ የድምጽ አሰጣጥ ሂደት በኋላ በእጩ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ስምምነት ላይ መድረስ ካልቻሉ በጸሎት አንድ ቀን እንዲቆዩ እና መራጭ ካርዲናሎች ነፃ ውይይት እንዲያደርጉ የሚያግዝ አጭር መንፈሳዊ ምክር በካርዲናል ዶሚኒክ ማምበርቲ መሪነት እንዲያገኙ ይፈቀድላቸዋል።

አዲሱ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት እንደተመረጡ ወዲያውኑ ምን ይከናወናል?

ካርዲናሎቹ አዲስ ርዕሥ ሊቃነ ጳጳሳትን ከመረጡ በኋላ ካርዲናል ዲያቆን ጠቅላላ የካርዲናሎች ጉባኤ ጸሐፊን እና ጳጳሳዊ የሥርዓተ አምልኮ አስተባባሪ አባትን ወደ ሲስቲን ጸሎት ቤት ይጠራቸዋል።

የካርዲናሎች ጉባኤ መሪ ብፁዕ ካርዲናል ጆቫኒ ባቲስታ ሬ ሁሉንም መራጮች በመወከል ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳትነት የተመረጡት እጩ ካርዲናል ይህን ሕገ ቀኖናዊ ምርጫን እንደሚቀበሉ ጠይቀው፥ መቀበላቸውንም ካረጋገጡ በኋላ በየትኛው ስም መጠራት እንደሚፈልጉ ይጠይቋቸዋል።

የጳጳሳዊ ሥርዓተ አምልኮ አስተባባሪ አባት ሁለት ምስክሮች ያረጋገጡትን የሠነድ ማረጋገጫን አዲሱ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ከመረጡት ስም ጋር በመዝገብ ውስጥ በመጻፍ ሠነድ ያዘጋጃሉ።

ከዚህ ቅጽበት ጀምሮ አዲስ የተመረጡት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት በዓለም አቀፉዊት ቤተ ክርስቲያን ላይ ሙሉ እና ከፍተኛ ስልጣንን ያገኛሉ። “ኮንክሌቭ” ወይም የካርዲናሎች ዝግ ጉባኤ ይህ ከሆነ በኋላ ወዲያውኑ ያበቃል።

ከዚያም መራጭ ካርዲናሎች አዲስ ለተመረጡት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ያላቸውን አክብሮት በመግለጽ ለመታዘዝም ቃል በመግባት እግዚአብሔርን ያመሰግናሉ።

ካርዲናል ዲያቆን በመቀጠል አዲስ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት መመረጣቸውን እንዲሁም ስማቸውን ለምእመናን እንዲህ በማለት በይፋ ያውጃሉ። “Annuntio vobis gaudium magnum; Habemus Papam.” ወይም “ታላቅ ደስታን እናበስራለን፤ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ተመርጠዋል!” በማለት በተለመደው መንገድ ያሳውቃሉ።

ወዲያውም አዲሱ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ የፊት ለፊት ሰገነት በኩል ለሮም ከተማ ነዋሪዎች እና ለመላው ዓለም ሐዋርያዊ ቡራኬያቸውን ይሰጣሉ።

የመጨረሻ ተግባር የሚሆነው፥ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት የምረቃ በዓል ማክበር ሲሆን አመቺ በሆነ ጊዜ ውስጥ አዲሱ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት የቅዱስ ዮሐንስ ዘላተራን ፓትርያርካዊ ሊቀ ባዚሊካን በመደበኛነት ተረክበው ሐዋርያዊ አገልግሎታቸውን በይፋ የሚጀምሩበት ይሆናል።

 

29 Apr 2025, 17:20