ፈልግ

የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ አስከሬን ሳጥን የማሸግ ሥነ-ሥርዓት የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ አስከሬን ሳጥን የማሸግ ሥነ-ሥርዓት  (VATICAN MEDIA Divisione Foto)

የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ አስከሬን ሳጥን ማሸግ በጸሎት ሥነ-ሥርዓት ተፈጸመ

ወደ 250,000 የሚገመቱ ሐዘንተኞች ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ያላቸውን አክብሮት ከገለጹ በኋላ ዓርብ አመሻሽ ላይ በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ውስጥ በተፈጸመው የጸሎት ሥነ-ሥርዓት አስከሬናቸው ታሽጓል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የቀብር ሥነ-ሥርዓታቸው ቅዳሜ ከመከናወኑ ቀደም ብሎ ዓርብ ሚያዝያ 17/2017 ዓ. ም. በጸሎት ሥነ-ሥርዓት የታሸገውን የቅዱስነታቸውን አስከሬን በርካታ ምዕመናን ጎብኝተው ሐዘናቸውን በመግለጽ ተሰናብተዋል።

አስከሬን የማልበስ ሥነ-ሥርዓት
አስከሬን የማልበስ ሥነ-ሥርዓት   (VATICAN MEDIA Divisione Foto)

አስከሬን የማሸግ ሥነ-ሥርዓት

የቅዱስነታቸው አስከሬን ባዚሊካ ውስጥ በዋናው መንበረ ታቦት ፊት በጵጵስና አልባሳት መቁጠሪያን በእጃቸው ይዘው ከእንጨት በተሰራ ሳጥን ውስጥ እንዲቀመጥ የተደረገው በርሳቸው ውሳኔ እንደ ነበር ታውቋል።

ዓርብ ዕለት የተከናወነውን የጸሎት ሥነ-ሥርዓት የመሩት የቅድስት መንበር የንብረት እና ፋይናንስ ክፍል አስተዳዳሪ ብፁዕ ካርዲናል ኬቨን ጆሴፍ ፋሬል፥ የጆርጅ ማሪዮ ቤርጎሊዮን የሕይወት ታሪክ እና በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳትነት ዓመታት ያከናወኗቸውን ተግባራት የሚዘረዝር ሠነድ በንባብ አሰምተዋል።

የ “266 ኛው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ተግባር በቤተ ክርስቲያን እና በሰው ልጆች ልብ ውስጥ ሲታሰብ ይኖራል” ሲል ሠነዱ ገልጿል። ከተጠቀሱት ክንውኖች መካከል እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ1980ዎቹ መጨረሻ በጀርመን አገር ያደረጉት ቆይታ እና በአርጀንቲና ያከናወናቸው ዘርፈ ብዙ ሥራዎች ሲሆኑ፥ በቦይነስ አይሬስ ሀገረ ስብከት ውስጥ ትሁት እና ተወዳጅ ሐዋርያዊ አባት እንደ ነበሩ፣ ወደ የቅርብ ይሁን የሩቅ አገልግሎታቸውን በሕዝብ ማመላለሻዎች በመጓዝ ይፈጽሙ እንደ ነበር፣ ለራሳቸው የሚሆን የዕለት ምግባቸውን እንደ መደበኛ ሰው ራሳቸው ያዘጋጁ እንደ ነበር ተገልጿል።

የአስከሬን ሳጥን ከታሸገ በኋላ
የአስከሬን ሳጥን ከታሸገ በኋላ   (Vatican Media)

የአስከሬናቸውን ፊት መሸፈን

ሊቀ ጳጳስ ዲዬጎ ራቬሊ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳስ ፍራንችስኮስ አስከሬን ፊት በነጭ የሐር ጨርቅ ካለበሱ በኋላ ብጹዕ ካርዲናል ፋረል የጸበል ውሃ የረጩ ሲሆን፥ በር ዕሠ ሊቃነ ጵጵስና ዓመታት ውስጥ ለማስታወሻነት የተሠሩ ሳንቲሞችን እና ሜዳሊያዎችን የያዘ ቦርሳ በአስከሬናቸው ሣጥን ውስጥ ተቀምጧል።

በአስከሬናቸው ሳጥን ውስጥ በተጨማሪም መስቀላቸው እና የጵጵስና አልባሳት፣ ስማቸው እና የሐዋርያዊ አገልግሎት ታሪካቸው የተጻፈበት ወረቀት ከተቀመጥ በኋላ ከእንጨት የተሠራው የአስከሬናቸው ሳጥን በዜማ ሥነ-ሥርዓት ታሽጓል።

 

 

26 Apr 2025, 10:19