የሐውልት ባለሙያው ቲሞቲ ሽማልዝ ነፍስሔር ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስን በተግባራቸው አስታወሰ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ካናዳዊው የቅርጻ ቅርጽ ባለሙያ ቲሞቲ ሽማልዝ በብርሃነ ትንሳኤው ማግሥት ሰኞ ወደ እግዚአብሔር ዘንድ የተመለሱትን እና የቀብር ሥነ-ሥርዓታቸውም ቅዳሜ ሚያዝያ 18/2017 ዓ. ም. የተፈፀመላቸውን የነፍስሔር ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጥልቅ አሳቢነት ቅርጽ ለማስያዝ ዕድል ማግኘቱን በቃለ ምልልሱ ገልጿል።
“የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት የቅርፃ-ቅርፅ ባለሙያ” እየተባለ የሚነገርለት የዕደ ጥበብ ሰው ቲሞቲ ሽማልዝ ሠላሳ ዓመታትን ያስቆጠረ እና የሠራቸው የጥበብ ሥራዎቹ ማኅበራዊ ጉዳዮችን የሚያሳዩ የነሐስ ቅርጻ ቅርጾች መሆናቸው ታውቋል። ቅዱሳት መጻሕፍትን እና የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስን ንግግሮች ወደ ምስላዊ የጥበብ ሥራዎች መለወጡ ተመልክቷል። በተለይም በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ በስተግራ በኩል የተቀመጠው የጥበብ ሥራው የተለያየ ባህል እና የዘር ልዩነት ያላቸውን ስደተኞችን እና ጥገኝነት ጠያቂዎችን የሚያሳይ የነሐስ ሐውልት እንደሆነ ተመልክቷል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳስት ፍራንችስኮስ ለተናቁት ሰዎች የሚሰጡትን ትኩረት የሚያስታውስ
በተጨማሪም የዕደ-ጥበብ ባለሙያው ሽማልዝ ከዘንድሮው የብርሃነ ትንሳኤው በዓል አስቀድሞ በነበረው ሳምንት በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ በተቀራኒው በኩል ያለውን “እንግዳ ተቀባይ መሆን” በሚል ርዕሥ የተዘጋጀውን ሐውልት የሰራ ሲሆን፥ ይህም በአግዳሚ ወንበር ላይ የሚገኝ ምስል ሲሆን ከአንድ ወገን ቤት አልባ ሰውን፣ በሌላኛው ወገን መልአክን የሚመስል ቅርጽ የሚያሳይ መሆኑ ተመልክቷል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ “መቅሠፍት” ብለው የገለጹትን እና ከዓለማችን መወገድ ያለበትን ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ችግር ላይ ትኩረት ያደረገ ሥራን ለእይታ ያቀረበ ሲሆን፥ “የተጨቆኑት ነጻ ይውጡ” የሚለው የሽማልዝ ሥራ ከሦስት ቶን በላይ የሚመዝን እና ሕገ-ወጥ የሰዎች አዝውውር ሰለባ ቅድስት ጆሴፊን ባኪታ እንደሚያካትት ታውቋል።
ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጋር ያለው ግንኙነት ከአሥር ዓመታት በፊት በሠራው “ቤት አልባው ኢየሱስ” ሐውልት መጀመሩን አስታውሶ፥ በዚያን ጊዜ “ክርስቶስን እንደ ቤት አልባ ሰው ማቅረብ “በጣም አክራሪነት ነው” ሲል ገልጾታል።
“በማቴዎስ ወንጌል ምዕ. 25 ላይ ከተጻፈው ጋር የሚስማማ እና የተቸገሩትን ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን በምናይበት ጊዜ ክርስቶስን ማየት አለብን” ሲል ተናግሯል። የቅርጻ ቅርጽ ባለሙያው ሽማልዝ፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ወደ ቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ መጥተው ሐውልቱን በእጃቸው በመንካት መባረካቸውን አስታውሷል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ብዙ ጊዜ በዓለም ዙሪያ የሚያደርጉት ይህ በመሆኑ ወቅቱ አስደናቂ እና ምሳሌያዊ ነበር ሲል ተናግሯል። ከዚህ በመነሳትም ያንን የቅዱስነታቸውን በጎ አድራጎት እና መንፈስ በሚያንፀባርቁ ብዙ ድንቅ ሥራዎችን ወደ ሕይወት ማምጣት መጀመሩን ሚስተር ሽማልዝ አብራርቷል።
አስደናቂ ገጠመኝ
“በቶሮንቶ ከተማ መሃል ቤት የሌለውን ሰው ካየሁ በኋላ ነው ያንን ሐውልት የሠራሁት” የሚለው ሚስተር ሽማልዝ፥ ይህም ኢየሱስ ክርስቶስ መሆን እንዳለበት ማሰቡን እና እና ሌሎች ሰዎች ኢየሱስን በተገለሉት እና በተናቁት ሰዎች መካከል እንዲያዩት መፈለጉን አስረድቷል።
ወቅቱ ጠቃሚ እንደ ነበር የገለጸው ሚስተር ሽማልዝ “ምክንያቱም በጊዜው አዲስ የተመረጡት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በማኅበረስቡ በተገለሉት ላይ በማትኮር ከዕይታችን የተሰወሩት ይፋ ወጥተው እንዲታዩ ያደረጉበት ትክክለኛ ወቅት ነበር” ሲል አስረድቷል።
እንዲያውም በሲኖዶስ ጉባኤ ወቅት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከጉባኤው አባላት ጋር ሐውልቱ ፊት ስደተኞችን፣ ጥገኝነት ጠያቂዎችን እና ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ሰለባዎችን በማስታወስ ጸሎት ማድረጋቸውን ሚስተር ሽማልዝ አስታውሷል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ተጋላጭ የሆኑትን ይንከባከባሉ
“በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ የሚቀመጥ ባለ ሃያ ጫማ ርዝመት ያለውን እና ስደተኞችን የሚገልጽ ግዙፉን ሐውልት እንድሰራ በተጠየቅሁ ጊዜ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የሚንከባከቧቸውን ተጋላጭ የሆኑትን በተጨባጭ ለዕይታ ማቅረብ ከባድ ነበር ያለው ሚስተር ሽማልዝ፥ ሐውልቱን ሠርቶ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ካስቀመጠው በኋላ በርካታ ሰዎች በእጆቻቸው ሲነኩ መመልከቱን ተናግሯል።
“ይህ ግዙፍ ሐውልት ከሠራኋቸው ሐውልቶች መካከል ትልቁ ይመስለኛል” የሚለው ሚስተር ሽማልዝ፥ ከዚህም ጋር ሌሎችም እስካሉ ድረስ፣ ሰዎችም ለማየት እስከቻሉ ድረስ የቅዱስነታቸውን ተግባር እና ለተቸገሩት ሰዎች ያደረጉትን እንክብካቤ ማስተዋወቅን ይቀጥላሉ” ሲል ተናግሯል።
ከወንጌሎች የተገኘ ተነሳሽነት
ሚስተር ሽማልዝ ከቫቲካን የዜና አገልግሎት ጋር ባደረገው ቃለ ምልልስ፥ የኪነ ጥበብ ሥራ ተግባር ሁል ጊዜም ዓላማን ማገልገል እንዳለበት ማመኑን ገልጾ፥ በዚህ ምክንያት የጥበብ ሥራ ውጤት ሊኖረው የሚችለው በሚወክለው ነገር ላይ የተመሠረተ እንደሆነ አስረድቷል።
“አስደናቂ የጥበብ ሥራ እንዲኖር ከተፈለገ ርዕሠ ሊኖረው ይገባል” ያለው ሚስተር ሽማልዝ፥ “የወንጌላትን ሃሳቦች በማጣመር እና ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሊያተኩሩባቸው የፈለጉትን ሃሳቦች ማክበር ለሥነ ጥበብ ሥራ ፍጹም ተስማሚ ነው” ብሏል።
በስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች ላይ የተሠራው ሐውልት ከተጠናቀቀ በኋላ በሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ላይ ትኩረት በማድረግ፣ በማጥናት ሃሳቦችን በማሰባሰብ ሐውልት መስራት እንዲጀምር ብፁዕ ካርዲናል ሚካኤል ቸርኒ ጥያቄ ማቅረባቸውን ገልጾ፥ ይህም ለቅዱስነታቸው ልብ ቅርብ ስለነበር ነው” በማለት አስረድቷል።
ቀጥሎ በነበረው ዓመት ከዕይታችን የተሰወሩት፣ በባሕላችን ውስጥ የተዘነጉ እና ለዘመናችን ባርነት የተጋለጡት ሰዎች መልክ ለማሳየት በመሞከር ሙሉ ጊዜን በመስጠት ለመሥራት ሞክሬያለህ” ሲል አስረድቷል።
በእነዚህ አስደናቂ ሥራዎች ውስጥ ከገባ በኋላ በዓለም ላይ መልካም ነገርን ለመሥራት ትልቅ የሥነ ጥበብ ሃላፊነት እንዳለበት የበለጠ መገንዘቡን ገልጿል።
በመጨረሻም፥ ይህንን ግምት ውስጥ በማስገባት የቅርጻ ቅርጽ ባለሙያው ቃለ ምልልሱን ሲያጠቃልል፥ “የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጥልቅ እና የአሳቢነት ዓላማን ለማሳካት ምክንያት አግኝቻለሁ” ብሏል።