የቅዳሜው የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የቀብር ሥነ ሥርዓት አከባበር
የዚህ ዘገባ አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን
ቅዳሜ ሚያዝያ 18/2017 ዓ.ም በሮም የሰዓት አቆጣጠር ከጠዋቱ 10፡00 ሰዓት ጀምሮ (በኢትዮጲያ የሰዓት አቆጣጠር ከቀኑ 05፡00 ሰዓት) ወደ 250 የሚጠጉ ካርዲናሎች፣ በርካታ ጳጳሳት፣ ካህናት፣ የሃይማኖት ተቋማት መሪዎች ወንድሞች እና እህቶች በቅዱስ አባታችን ፍራንችስኮስ የቀብር ሥነ ሥርዓት ላይ ይገኛሉ። አርብ አመሻሽ ላይ የታሸገው የሟቹ የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት በእንጨት እና በዚንክ የተሰራ የሬሳ ሳጥን በዱስ ጴጥሮስ ባሲሊካ በመሠዊያው ፊት ለፊት ይቀመጣል። ከሁሉም ጂኦግራፊያዊ ፣ማህበራዊ ፣ፖለቲካዊ እና ባህላዊ ዳራዎች የተውጣጡ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የመጨረሻውን የክብር ስንብት የሚጠበቁ እጅግ ብዙ ሰዎች በእዚያ ሥፍራ ይገኛሉ። ይህ የተለያየ ሕዝብ ንፍስዕር ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ቤተክርስቲያንን ይወክላሉ፣ እርሳቸው ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ ደጋግመው እንደገለፁት "ሁሉንም ሰው፣ ሁሉም ሰው፣ ሁሉም ሰው" የቤተ ክርስቲያን አካል እንደ ሆነ ደጋግመው መናገራቸው ይታወሳል።
የኖቪና (የዘጠኝ ቀን) የመጀመሪያ ቅዳሴ
የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳትን የቀብር ሥነ-ሥረዓት ደንብ በሚገልጸው ሰነድ ላይ እንደተደነገገው፣ የቀብር ሥነ ሥርዓቱ በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ እስከ እሁድ ሚያዝያ 26/2017 ዓ.ም ቀን በቀን ከሚደረጉ ዘጠኝ ቅዳሴዎች የመጀመሪያው ነው። የቀብር ሥነ ሥርዓቱ የሚመራው በካርዲናል ጆቫኒ ባቲስታ ሬ፣ የካርዲናሎች ኮሌጅ ዲን ነው።
ቅዳሴው ከሐዋርያት ሥራ፣ ከቅዱስ ጳውሎስ መልእክት እና የዮሐንስ ወንጌል ንባብን ይጨምራል። በብፁዕ የካርዲናሎች ኮሌጅ ዲን የተዘጋጀው ይህ ስብከት፣ የምዕመናን ጸሎት በማስከተል እና የመጨረሻው የምስጋና ሥነ ሥርዓት በፊት ምእመናን በፈረንሳይኛ፣ በአረብኛ፣ በፖርቹጋልኛ፣ በፖላንድኛ፣ በጀርመንኛ እና በቻይንኛ ቋንቋ ጸሎት ይደረጋል።
ሥነ-ሥረዓቱ ለመጨረሻ ጊዜ ለንፍስዕር ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመዘመር የሲስቲን የጸሎት ቤት መዘምራን ታጅቦ ይቀርባል።
ወደ ቅድስት ማርያም ሜጀር
በቀድሞ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ መንፈሳዊ ኑዛዜ መሠረት የሬሳ ሳጥኑ ወደ ቅድስት ማርያም ሜጀር የጳጳስ ባዚሊካ ይወሰዳል። የቀብር ሥነ ሥርዓቱ በመዲናዋ ጎዳናዎች ላይ በዝግታ በሚደረግ ዑደት የሚከናወን ሲሆን ወደ አራት ኪሎ ሜትር ርቀት ይሸፍናል።
ይህ ጉዞ ሮማውያን ከ47ቱ የቅዱስነታቸው ሐዋርያዊ ጉዞዎች በፊትና በኋላ፣ እና በቅርቡም በየካቲት እና መጋቢት ወር ሆስፒታል ከቆዩ በኋላ "Virgin Salus Populi Romani " (የሮም ሕዝቦች ጠባቂ) በሆናችው በእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ምስል ፊት ለመጸለይ በሚወስደው መንገድ ጳጳሳቸውን እንዲሰናበቱ ያስችላቸዋል።
አስክሬናቸው ወደ ቅድስት ድንግል ማርያም ሜጀር ባዚሊካ ሲደርስ አሁንም በሲስቲን የጸሎት ቤት መዘምራን እና በመዝሙሮች በመታጀብ፣ የሬሳ ሳጥኑ “የመጨረሻዎቹ” በቅድሞ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ልብ ውስጥ ሁልጊዜ ልዩ ቦታ የነበራቸው ድሆች እና የተገለሉ ሰዎች ይቀበሉታል። የሬሳ ሳጥኑ ወደ ቅድስት ማርያም ሜጀር መሠዊያ መንበረ ታቦት ከመወሰዱ በፊት የመጨረሻውን ግብር የሚካፈሉ ይሆናሉ። የቀብር ሥነ ሥርዓቱ በዚያው ይከናወናል።
ብፁዕ ካርዲናል ፋሬል (የሐዋርያዊ መንበር ንብረቶችን እና መብቶችን የመቆጣጠር እና የማስተዳደር ተግባር ያላቸው) ካርዲናል ኬቨን ፋሬል፣ የጳጳሱን ቤተ መቅደስ አስተዳደር፣ የሥርዓተ አምልኮ እና ጳጳሳዊ ክብረ በዓላት አዘጋጅ ጽ/ቤት ኃላፊን ጨምሮ የሬሳ ሣጥኑን በማኅተም ምልክት ያደርጉበታል።
የጴጥሮስ ተተኪ አስክሬን በመቃብር ውስጥ ይቀመጣል እና በጸበል ውሃ ይረጫል። በላቲን ቋንቋ ከ"ሬጂና ቼሊ" ጸሎት በኋላ፣ የቅድስት ማርያም ሜጀር ቆመስ የቀብር ሥነ ሥርዓቱን የሚያረጋግጥ ኦፊሴላዊ ተግባር ያደርጋል እና በስፍራው ለተገኙት ሰዎች ሁሉ ጮክ ብሎ ያነባል። ሰነዱ በካሜርሌንጎ ካርዲናል፣ የጳጳሱ ቤተሰብ አስተዳዳሪ፣ የጳጳሳዊ ሥርዓተ ቅዳሴ በዓላት መምህር በመጨረሻም ይፈርማል።
ስነ-ስርዓቱ በሮም የሰዓት አቆጣጠር ከቀኑ 2፡00 ሰዓት (በኢትዮጲያ የሰዓት አቆጣጠር ከሰዓት በኋላ 9፡00) አካባቢ ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል።
ዓለም በሮም
የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የቀብር ሥነ ሥርዓት በዓለም አቀፍ ደረጃ ይተላለፋል። በቫቲካን መገናኛ ብዙኃን የፌስቡክ ገጽ ላይ በቫቲካን ኒውስ፣ በቫቲካን መገናኛ ብዙኃን ዩቲዩብ ቻናል ላይ ከእንግሊዝኛ ማብራሪያ ጋር ይቀርባል።
ከ130 ያላነሱ ሀገራት እና አለም አቀፍ ድርጅቶች 12 ነገስታት እና 55 የሀገር መሪዎች፣ 14 የመንግስት መሪዎች እና ሌሎች ከፍተኛ ባለስልጣናትን ጨምሮ ልዑካን በቀብር ሥነ-ሥርዓቱ ላይ እንደ ሚገኙ ይጠበቃሉ። ዝግጅቱን ለመዘገብ ከ4,000 በላይ ጋዜጠኞች የቅድስት መንበር ዕውቅና ጠይቀዋል።
የቀድሞ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ 266ኛ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት የነበሩ ሲሆን ላለፉት 12 አመታት ያህል አለማቀፋዊቷን የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን በቅንነት እና በታማኝነት መምራተቸው የሚታወቃል፣ በ88 አመታቸው በሚያዚያ 13/2017 ዓ.ም ከዚህ አለም ድካም በሞት መለየታቸው ይታወቃል፣ ነብሳቸውን እግዚአብሔር በአብርሃም፣ በይሳቅ እና በያዕቆብ አጠገብ ያኖርልን ዘንድ ጸሎታችን እና ምኞታችን ነው።