“በምናባዊው ዓለም ውስጥ ሆነው በአካል የመገኘት አስፈላጊነት”
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
“ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ ለሕሙማን እና ለጤና ባለሞያዎች በተዘጋጀው የኢዮቤልዩ በዓል መስዋዕተ ቅዳሴ ሥነ-ሥርዓት ፍጻሜ ላይ በድንገት መገኘት ትርጉም ያለው መልዕክት ነው።
በምናባዊ ዓለም ውስጥ ሁሉን ነገር በማኅበራዊ መገናኛዎች መስኮት በኩል መከታተል በምንችልበት በዚህ ወቅት ቅዱስነታቸው በምዕመናን መካከል በአካል መገኘታቸው የበለጠ አስፈላጊ ነበር።
ሰዎች በሚገኙበት ሥፍራ ለመሆን፣ ወደ እነርሱ በአካል ለመቅረብ ጥረት በማድረግ እና አብሯቸው መሆን ከነጋዲያን መካከል አንዱ ለመሆን ያስችላል።
የሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ ተተኪ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እሁድ ዕለት በምዕመናን መካከል በድንገት በመታየታቸው፥ በአካል መገኘትን ምንም ነገር ሊተካው እንደማይችል ያሳያል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ምንም እንኳን በመተንፈሻ መሣሪያ ቢታገዙ እና ድምጻቸው ደካማ ቢሆንም በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ፊት ለፊት ከተሰበሰቡት ምዕመናን ጋር መሆን መፈለጋቸው በራሱ ከቃላት በላይ ትርጉም ያለው መልዕክት ነው።
የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሁለተኛው መልዕክት፥ ከጄሜሊ ሆስፒታል ከወጡ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በአደባባይ ተገኝተው የሕሙማን እና የጤና ባለሞያዎች ኢዮቤልዩን ለማክበር መወሰናቸው ነው። ይህም ለሕሙማን እና እነርሱን ለሚንከባከቡ ሰዎች ያላቸውን ቅርበት የገለጹበት ነው።
ጤናቸውን በተመለከተ አሁን የሚያሰጋ ነገር ባይኖርም ቅዱስነታቸው አሁንም የሕመም ምልክቶች ይታይባቸዋል። ከደካሞች መካከል አንዱ በመሆን፥ በሺዎች የሚቆጠሩ ምዕመናን በየቀኑ እንደሚያደርጉት ሁሉ ወደ ቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካው በቅዱስ በር በኩል በማለፍ እና ኑዛዜን በመግባት የኢዮቤልዩ በዓላቸውን ማክበርን አልተውም።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በሳንባ ምች ምክንያት ሕመም ቢሰማቸውም የኢዮቤልዩ ዓመት መግቢያን ምክንያት በማድረግ በብርሃነ ልደቱ ምሽት በከፈቱት ቅዱስ በር በኩል ወደ ባዚሊካው ገብተዋል።
እሁድ መጋቢት 28/2017 ዓ. ም. ጠዋት የፈጸሙት አስገራሚ ተግባር፥ መጋቢው ከመንጋው ጋር፣ ጳጳስም ከምዕመኑ ጋር ያለውን ግንኙነት እንድናውቅ አድርጎናል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በማገገም ላይ ቢሆኑም፣ የዶክተሮች ማስጠንቀቂያ ቢኖርም፣ ወደ ውጭ መውጣት በጤናቸው ላይ ሊያስከትል የሚችለው አደጋ መኖሩን ቢገነዘቡትም ከሕዝበ እግዚአብሔር እና ከመንጋቸው ጋር በይፋ መገናኘትን አላቋረጡም።
ይህን በማድረጋቸው ሰዎች ሆስፒታል ሲገቡ፣ በወረርሽኝ ምክንያት ቤት ውስጥ እንዲቆዩ ሲገደዱ ወይም ከቦታ ቦታ መጓዝ ሳይችሉ ሲቀር የሚጠቀሙት ምናባዊ አካሄድ በአካል ከመገናኘት ጋር የማይስተካከል መሆኑን አሳይተውናል።
ከአንድ ዓመት በፊት ባደረጉት ንግግርም፥ “ፍቅር ተጨባጭነትን፣ እርስ በርስ በአካል መገናኘትን፣ ጊዜ እና ቦታ መስጠትን ይፈልጋል፤ ከሩቅ ሆነው በማኅበራዊ መገናኛዎች በኩል ከሚያደመጡት ውብ ቃላት ወይም ከሚመለከቱት ማራኪ ምስሎች ጋር ሊወዳደር ፈጽሞ አይችልም” ማለታቸው ይታወሳል።
ይህ ደግሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለሕዝብ እግዚአብሔር ያላቸውን ፍቅር በቃላት ብቻ ሳይሆን ዘወትር በተጨባጭ ድርጊት እና ርህራሄ መግለጻቸውን ያመለከታል።”