ፈልግ

በኢንዶኔዥያ ውስጥ ለእጽዋዕት የሚደረግ እንክብካቤ በኢንዶኔዥያ ውስጥ ለእጽዋዕት የሚደረግ እንክብካቤ  

“የሰላም እና የተስፋ ዘሮች” የሚለው የዓለም አቀፍ የፍጥረት እንክብካቤ ቀን ጭብጥ መሆኑ ተገለጸ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ ዘንድሮ ነሐሴ 26/2017 ዓ. ም. ለሚከበረው ዓለም አቀፍ የፍጥረት እንክብካቤ የጸሎት ቀን፥ “የሰላም እና የተስፋ ዘሮች” የሚል መሪ ቃል መምረጣቸውን በቅድስት መንበር የሰው ልጅ ሁለንተናዊ ዕድገት አገልግሎት አስተባባሪ ጽሕፈት ቤት አስታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የዘንድሮው ዓለም አቀፍ የፍጥረት እንክብካቤ የጸሎት ቀን የሚከበረው በተያዘው የኢዮቤልዩ ዓመት ሲሆን፥ “ውዳሴ ላንተ ይሁን” የሚለው ሐዋርያዊ ቃለ-ምዕዳን አሥረኛ ዓመት መታሰቢያ ወቅትም እንደሆነ ታውቋል።   

“የሰላም እና የተስፋ ዘሮች” የሚለው የዘንድሮው ዓለም አቀፍ የፍጥረት እንክብካቤ የጸሎት መሪ ሃስብ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የመረጡት እንደሆነ ታውቋል።

በየዓመቱ ከነሐሴ 26 ጀምሮ እስከ የቅዱስ ፍራንችስኮስ ዓመታዊ በዓል ድረስ ማለትም መስከረም 24 ድረስ የሚከበረው ዓለም አቀፍ የፍጥረት እንክብካቤ የጸሎት ቀን የሚዘጋጀው በአብያተ ክርስቲያናት አንድነት ተነሳሽነት እንደሆነ ይታወቃል።

በቅድስት መንበር የሰው ልጅ ሁለንተናዊ ዕድገት አገልግሎት አስተባባሪ ጽሕፈት ቤት ሰኞ መጋቢት 29/2017 ዓ. ም. በሰጠው መግለጫ፥ ለዘንድሮው የፍጥረት ሰሞን የተመረጠው መሪ ሃሳብ “ሰላም ከፍጥረት ጋር” የሚል እና መጽሐፍ ቅዱሳዊ ማጣቀሻውም በትንቢተ ኢሳያስ ምዕ. 32፡14–18 ላይ ከተጻፈው የተወሰደ መሆኑን አስታውቋል።

በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እና ባለፉት ዓመታት ውስጥ በነበሩት ርዕሣነ ሊቃነ ጳጳሳት ሐዋርያዊ አስተምህሮች ላይ እንደተገለጸው ሁሉ፥ ለፍጥረት የሚሰጥ ሰላም እና እንክብካቤ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ1990 እና 2010 ዓ. ም. ከተጻፉ ዓለም አቀፍ የሰላም ቀን ሐዋርያዊ መልዕክቶች ጋር የቅርብ ትስስር እንዳለው ተመልክቷል።

እንደዚሁም በጦርነት አደጋ እና በምድራችን ጥፋት መካከል ያለውን ግንኙነት የሚገልጽ የሃብት ውድመት እና የጦር መሣሪያዎች ምርት ዕድገትን ያመላክታል።

በቅድስት መንበር የሰው ልጅ ሁለንተናዊ ዕድገት አገልግሎት አስተባባሪ ጽሕፈት ቤት መግለጫ ከዚህም ጋር ክርስቲያኖች ተስፋን የሚሰጥ ዘላቂ የጋራ ሰላም ለማምጣት ምቹ ሁኔታዎችን እንዲያመቻቹ እና አብረው እንዲጸልዩ ጋብዟል።

የዘሩ ምሳሌም ሰላምን ለማምጣት የረዥም ጊዜ ቁርጠኝነት እንደሚያስፈልግ የሚያመላክት ሲሆን፥ ይህ የሚሆን ከሆነ በሁሉም አህጉራት መካከል የሰላም ዘሮች በቅለው ሊታዩ እንደሚችሉ ያለውን እምነት ገልጿል።

 

08 Apr 2025, 17:18