ብጹዓን ካርዲናሎች ምዕመናን የአዲሱን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ምርጫ በጸሎት እንዲደግፉት ጠየቁ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ረቡዕ ሚያዝያ 22/2017 ዓ. ም. ይፋ የሆነው የቅድስት መንበር መግለጫ፥ ቀጣዩን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት የሚመርጡበትን ዝግ ጉባኤ ለማካሄድ ዝግጅት ላይ የሚገኙት ብጹዓን ካርዲናሎች፥ ምዕመናን በጸሎታቸው እንዲያግዟቸው መጠየቃቸውን አስታውቋል።
በቫቲካን ጠቅላላ ስብሰባውን በማካሄድ ላይ የሚገኘው የካርዲናሎች ጠቅላላ ጉባኤ፥ “የእግዚአብሔር ሕዝብ ይህን ልዩ የቤተ ክርስቲያን ክንውን እንደ ጸጋ ተቀብሎ በጸሎት እና በማስተዋል የእግዚአብሔርን ፈቃድ እንዲያዳምጥ” በማለት መጋበዙን መግለጫው አስነብቧል።
ብጹዓን ካርዲናሎቹ “ቀጣዩን የቅዱስ ጴጥሮስ ተተኪን የመምረጥ ሃላፊነት እንዳለብን ስለምናውቅ የመላው ምእመናን የጸሎት ድጋፍ እንደሚያስፈልገን ይሰማናል” ሲሉ ገልጸዋል።
ጸሎት “በቤተ ክርስቲያናችን ውስጥ ሁሉንም የኢየሱስ ክርስቶስ አካል የሆኑትን አንድነት የሚያበረታታ እውነተኛው ኃይል ነው” ሲሉ አክለዋል።
“ለመንፈስ ቅዱስ ተግባር ታዛዦች በመሆን ከፊታችን ለሚጠብቀን ትልቅ ተግባር እና ከጊዜው አጣዳፊነት ጋር ከሁሉ አስቀድሞ ራሳችንን ማለቂያ ለሌለው ለሰማዩ አባታችን ጥበብ እና ትኅትና መሣሪያ ማድረግ አለብን” ብለዋል።
ብፁዓን ካርዲናሎቹ በመግለጫቸው፥ “መንፈስ ቅዱስ ለቤተ ክርስቲያን የሚናገረውን መስማት ለሚገባው የእግዚአብሔር ሕዝብ ሕይወት ዋና ተዋናይ ነው” በማለት አስገንዝበዋል።
ብጹዓን ካርዲናሎቹ በመጨረሻም፥ “እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በእናትነት አማላጅነቷ ጸሎቶቻችንን ትቀበልልን” በማለት መግለጫቸውን ደምድመዋል።