ካርዲናሎች ለር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ የቀብር ሥነ-ሥርዓት ታዳሚዎች እና አዘጋጆች ምስጋናቸው አቀረቡ
የብጹዓን ካርዲናሎች ጠቅላላ ጉባኤ ያለፈው ቅዳሜ ሚያዝያ 18/2017 ዓ. ም. በቫቲካን ውስጥ በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ በተፈጸመው የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የቀብር ሥነ-ሥርዓት መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ ለተገኙት የሃይማኖት እና የፖለቲካ መሪዎች እንዲሁም ሥነ-ሥርዓቱን በማስተባበር እገዛ ላደረጉት ሲቪል ባለስልጣናት ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ጉባኤው በመግለጫው፥ ያለፈው ቅዳሜ በተፈጸመው ሥነ-ሥርዓት ላይ የተገኙትን የአብያተ ክርስቲያናት መሪዎች፥ የእስልምና፣ የአይሁድ እና የሌሎች እምነት ተወካዮችን፣ የሀገር መሪዎችንን እና የመንግሥት ልዑካንን በሙሉ አመስግኗል።
የብጹዓን ካርዲናሎች ጠቅላላ ጉባኤ በቅድስት መንበር መግለጫ ክፍል በኩል ባስተላለፈው መልዕክት፥ በተለይም ለቤተ ክርስቲያኒቱ ክብርን በመስጠት በመስዋዕተ ቅዳሴው ሥነ-ሥርዓት ላይ የተገኙት እና ነፍስሔር ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለእምነት፣ ለሰላም እና ለወንድማማችነት ያሳዩትን የማያቋርጥ ቁርጠኝነት በማስታወስ የቅድስት መንበርን ሐዘን በመጋራታቸው ምስጋናውን አቅርቧል።
የካርዲናሎች ጠቅላላ ጉባኤ በተጨማሪም የቅድስት መንበር እና የቫቲካን ከተማ ጠቅላይ ግዛት ሠራተኞችን ጨምሮ፥ ሥነ-ሥርዓቱ በተሳካ ሁኔታ እንዲፈጸም አስተዋጽዖን ያበረከቱ የጣሊያን መንግሥትን፣ የሮም ከተማ አስተዳደርን፣ የጸጥታ አስከባሪዎችን፣ የመከላከያ ኃይልን እና የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎችን አመስግኗል።
ጉባኤው እንደዚሁም በሳምንቱ መጨረሻ ላይ በመስዋዕተ ቅዳሴው ሥነ-ሥርዓት ላይ የተሳተፉ አዳጊ ወጣቶችን በማመስገን፥ “ቤተ ክርስቲያን ከሙታን በተነሳው በኢየሱስ ክርስቶስ ኃይል ሕያው ሆና ትኖራለች” በማለት መግለጫውን ደምድሟል።
01 May 2025, 11:19