ብጹእ አቡነ ማርቲኔሊ በጦርነት የተጎዳው የየመን ህዝብ 'ጥልቅ ስቃይ' እንደሚሰማቸው ገለጹ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
በደቡባዊ አረቢያ ከፍተኛ የቤተክርስቲያን መሪ የሆኑት የካፑቺን ማህበር ጳጳስ ብጹእ አቡነ ፓኦሎ ማርቲኔሊ በየመን እየተካሄደ ያለው ግጭት ተባብሶ በመቀጠሉ ያደረባቸውን ስጋት ገልጸዋል። አሜሪካ የሁቲ አማፂያን በቀይ ባህር መከቦች ላይ የሚያደርሱትን ጥቃት ለማስቆም የሚደረገው ጥረት አካል ነው ያለችውን 'ወሳኝ እና የማያዳግም' የአየር ጥቃት ከባለፈው ቅዳሜ ጀምራ እየፈጸመች መሆኑን ተናግራለች።
በእስራኤል እና በሃማስ መካከል ለሚካሄደው ጦርነት ሁቲዎች ሃማስን በመደገፍ በቀይ ባህር ላይ በሚመላለሱ መርከቦች ላይ ባደረሱት ጥቃት እና በእስራኤል ኢላማዎች ላይ ባደረሱት የባለስቲክ ሚሳኤል ጥቃት አፀፋዊ ምላሽ ለመስጠት የአሜሪካ ጦር ሃይሎች ባደረሱት የአየር ጥቃት ከ100 በላይ ሰዎች ሞተዋል። የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የሁቲ አማፂያንን ሙሉ በሙሉ እንደሚያጠፉ መዛታቸው የሚታወስ ነው።
በሃማስ እና በእስራኤል መካከል እየተካሄደ ያለው ግጭት በ 2006 ዓ.ም. የሁቲ አማፂያን የየመን ዋና ከተማዋን ሰነዓን ሲቆጣጠሩ የተጀመረውን የእርስ በእርስ ጦርነት ለማስቆም የሚደረገውን ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶችን እንዳወሳሰበ የሚነገር ሲሆን፥ የእርስ በርስ ጦርነቱ በወቅቱ “በዓለም ላይ ከታዩት እጅግ የከፋ ሰብዓዊ ቀውሶች ውስጥ ትልቁ ነው” ተብሎ መገለጹ ይታወቃል። በጦርነቱ እስከ 400,000 የሚደርሱ ሰዎች እንደሞቱ የሚታመን ሲሆን፥ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ደግሞ ከቀያቸው ተፈናቅለው በከፍተኛ ረሃብ፣ ድህነት እና በሽታ እየተሰቃዩ ይገኛሉ።
ሁቲዎች እስራኤል በሃማስ ላይ የጣለችውን እገዳ እስከምታነሳ ድረስ በቀይ ባህር ላይ በሚንቀሳቀሱ መርከቦች ላይ ማነጣጠራቸውን እንደሚቀጥሉ እና ጦሩ ለጥቃቱ ምላሽ እንደሚሰጥ አስታውቀዋል።
በጣም ደካማ ቡድኖች ከፍተኛ ዋጋ ይከፍላሉ
ብጹእ አቡነ ማርቲኔሊ “በከፍተኛ የደህንነት ችግር ምክንያት ሁኔታውን ሊለውጡ እና በመጨረሻም አዲስ ጅማሮ ሊያስጀምሩ የሚችሉ የሰብአዊ እርዳታ ፕሮጀክቶችን ማከናወን ከባድ ነው” ሲሉ የጸጥታ ሁኔታ ከባድ እንደሆነ የገለጹ ሲሆን፥ “እንዲህ ባለች ውብ ሀገር ውስጥ ሰዎች እንደዚህ በድህነት ሲሰቃዩ ማየት እና ማሰቡ ለከባድ ስቃይ እና ጭንቀት ይዳርጋል” በማለት የችግሩን ጥልቀት አብራርተዋል።
ሃዋሪያዊ አስተዳደሩ በማከልም በተለይ ህጻናትን ጨምሮ በጣም ደካማ የሆኑት ቡድኖች ከፍተኛ ዋጋ የሚከፍሉ መሆናቸውን በመግለጽ፥ ከሦስት ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ የአገር ውስጥ ተፈናቃይ የመናዊያን ሕፃናት በከፍተኛ ድህነት እና ረሃብ ውስጥ እንደሚገኙ እና የኮሌራ ወረርሽኝን ጨምሮ ለተለያዩ በሽታዎች እንደተጋለጡ አስረድተዋል።
“የከፍተኛ ስቃይ መንስኤ ነው”
በመንግስት እና በአማፂ ሃይሎች መካከል እርቅ የተካሄደ ቢመስልም፥ በእስራኤል እና በሃማስ መካከል የተካሄደው የተኩስ አቁም “የተረጋጋ እና ጥንቃቄ የተሞላበት ብሩህ ተስፋን የሚሰጥ ነበር” ሲሉ ብጹእ አቡነ ማርቲኔሊ የገለጹ ሲሆን፥ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሁቲዎችን “አሸባሪዎች” ብለው ለማወጅ መወሰናቸው በሰሜን የመን ላይ ያለውን ነገር ይበልጥ እንዳወሳሰበው በመጠቆም፥ “ግልጽ እና መጠነ ሰፊ ግጭቶች በሲቪሎች ላይ ሊያስከትሉ የሚችሉትን ከባድ አደጋዎች ማሰብ የከባድ ስቃይ መንስኤ ይሆናል” ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
ብጹእነታቸው በመጨረሻም የየመን ሕዝብ ለአሥር ዓመታት የዘለቀው የእርስ በርስ ጦርነት መከራ እንደሆነበት ገልጸው፥ “አጠቃላይ ጦርነት ሲከሰት ብቻ ሳይሆን አሁንም የሕዝቡን ስቃይ መገመት ይቻላል” ብለዋል።