ፈልግ

በማያንማር የተከሰተው ከባድ የመሬት መንቀጥቀጥ ያስከተለው ውድመት በማያንማር የተከሰተው ከባድ የመሬት መንቀጥቀጥ ያስከተለው ውድመት 

ማያንማር በመሬት መንቀጥቀጥ በመጎዳቷ ከፍተኛ ዕርዳታን እንደምትፈልግ ተገለጸ

በማያንማር የተከሰተው ከባድ የመሬት መንቀጥቀጥ ቀድሞውንም ያለውን አስከፊ ሰብዓዊ ቀውስ ማባባሱ ተገለጸ። በእንግሊዝ “የበርማ ዘመቻ” የተሰኘ የዕርዳታ ማስተባበሪያ ዳይሬክተር ማርክ ፋርማነር፥ በእርስ በርስ ግጭት በተጎዳች ማያንማር ውስጥ ባለው የዕርዳታ ገደቦች ዙሪያ ያለውን ውስብስብ እውነታ ከቫቲካን መገናኛ ጋር በነበራቸው ቆይታ አብራርተዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ከደቡብ ምሥራቅ እስያ የሚወጡት ምስሎች ከፍተኛ ውድመት መድረሱን ያሳያሉ። ዓርብ መጋቢት 19/2017 ዓ. ም. በማያናማር እና ታይላንድ ውስጥ የተከሰተው የመሬት መንቀጥቀጥ ያስከፈለውን ዋጋ በግልፅ ለማየት ቢከብድም፥ ሁኔታው ​​​​በጣም አሳሳቢ እና የሰብዓዊ ዕርዳታ አስፈላጊነት ከፍተኛ መሆኑ ታውቋል።

በሬክተር መለኪያ 7.7 የደረሰው የመሬት መንቀጥቀጥ እና በኋላም የተከሰቱት አራት መንቀጥቀጦች የማያንማርን ማዕከላዊ ክልሎች ማለትም ማንዳላይን እና ናይፒዳው እንዲሁም ደቡባዊ ክልል ሳጋንግን ማናወጡ ታውቋል። ሆስፒታሎችን ጨምሮ በመሠረተ ልማት እና በመኖሪያ ቤቶች ላይ የደረሰው ውድመት ኅብረተሰቡን ለጭንቀት መዳረጉ ታውቋል። የፖለቲካ አለመረጋጋት እና የእርስ በርስ ጦርነት ባለባት ማያንማር ውስጥ በግጭቶች ሳቢያ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በስደተኞች መጠለያ ካምፖች ውስጥ እየኖሩ ባሉበት ወቅት እንዲህ ዓይነቱ አደጋ ለመረዳት የማይቻል ውድመት ማስከተል ታውቋል።

ከጉዳት የተረፈ አንድም አካባቢ የለም

የበርማ ዘመቻ ዩኬ ዳይሬክተር ማርክ ፋርማነር ከቫቲካን ዜና ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፥ በአደጋው ​​ዙሪያ ያለውን ውስብስብ ሁኔታ በማረጋገጥ፥ ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የሚደርሱ ዘገባዎች ከአደጋው የተረፈ የትኛውም አካባቢ እንደሌለ መግለጻቸውን ተናግረው፥ አደጋው ያደረሰው ተጽእኖው ከትላልቅ ከተሞች እስከ ሩቅ መንደሮች ጭምር እንዲሁም በቀርከሃ ቤቶች ውስጥ የሚኖሩ ወይም በታይላንድ የስደተኞች ካምፖች ውስጥ የሚኖሩ ሰዎችን ለከፋ ችግር ማጋለጡን አስረድተዋል።

የጉዳቱ መጠን ያጋጠሙ ተግዳሮቶችን በማሳየት የበርማ ወታደሮች በመረጃ ላይ ጥብቅ ቁጥጥር ሲያደርጉ የቆዩበትን የፖለቲካ ሁኔታ እንደሚገልጽ ተነግሯል። “ሠራዊቱ ትክክለኛ አሃዞችን በጭራሽ አይናገርም” ያሉት ማርክ ፋርማነር፥ አሁን ሰፋፊ የሀገሪቱ ክፍሎች በእጃቸው ላይ ባለመሆኑ መረጃዎች እየወጡ እንደሚገኙ ገልጸው፥ በተለያዩ ክልሎች ውስጥ የሚሠሩ በርካታ አስተዳደሮች ለዚህ ቀውስ ውጤታማ ምላሽ መስጠት ትልቅ ፈተና ሆኖባቸዋል” ሲሉ አስረድተዋል።

አደጋው በተጋላጭ ሰዎች ላይ ያስከተለው ተጽእኖ

እንደ ጎርጎሮሳውያን በ2021 ዓ. ም. የተካሄደውን መፈንቅለ መንግሥት ተከትሎ የተወሰደው ወታደራዊ እርምጃ ብዙዎችን በማፈናቀሉ የስደተኞችን ጉዳይ ውስብስብ ማድረጉ ታውቋል። በተለይም በምሥራቅ በርማ ተራራማ አካባቢዎች ጉዳዩ አሳሳቢ ሲሆን፥ “በዝናብ ወቅት የተከሰተው የመሬት መደርመስ በካምፖች የሚኖሩ ወደ ሁለት ሚሊዮን የሚደርሱ ተፈናቃዮችን አደጋ ላይ ጥሏል” ሲሉ ማርክ ፋርማነር ተናግረው፥ በወታደሮች የተጣሉት የግንኙነት ገደቦች ትክክለኛ መረጃን ለመሰብሰብ ወይም ዕርዳታን ለመላክ የሚደረገውን ጥረት ማደናቀፉን ገልጸዋል።

የዕርዳታ አቅርቦትን ማገድ

“በጦር ኃይሉ የሚጣሉ ተጨማሪ ገደቦች በዕርዳታ አቅርቦት ላይ ተጽእኖ ማሳደራቸው የማይቀር ነው” ያሉት ማርክ ፋርማንር፥ “ወታደራዊ አገዛዝ በዓለም ላይ በዕርዳታ አሰጣጥ ላይ አንዳንድ ከባድ ገደቦችን እንደሚጥል አስረድተው፥ በዚህም ምክንያት ለመሬት መንቀጥቀጥ የሚሰጥ ምላሽ አዝጋሚ እንደሚሆን፥ በተለይ በሕይወት የተቀበሩ እና በፍርስራሾች ውስጥ የተያዙ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ሕይወት ቶሎ ማዳን አስቸጋሪ እንደሚሆነ አስረድተዋል።

ጉዳዩን ይበልጥ ውስብስብ የሚያደርገው የአገሪቱ ሰፊ ክፍሎች በተለያዩ ተቃዋሚ ሃይሎች እና የጎሳ ሚሊሻዎች ቁጥጥር ስር መሆኑን የገለጹት ማርክ ፋርማንር፥ በዚህ ምክንያት ዓለም አቀፍ የዕርዳታ ድርጅቶች ከመንግሥት ጋር በመተባበር መሥራት እንደማይችሉ፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ኤጀንሲዎችን እና ሌሎችም አባሎቻቸውን ወደ ተለያዩ ቦታዎች መላክ እንደማይችሉ አስረድተዋል። የበርማ ጦር ሠራዊት ዛሬም ቢሆን በመሬት መንቀጥቀጡ በተመቱ አካባቢዎች የአየር ድብደባ እየፈፀመ በመሆኑ ዓለም አቀፍ ቡድኖች ወደ ሥፍራው ለመግባት ፍቃደኛ እንደማይሆኑ አስረድተዋል።

ስለዚህ በመሬት መንቀጥቀጥ የተጎዱ ሰዎችን ለመርዳት በቂ የገንዘብ ድጋፎች በአገር ውስጥ ድርጅቶች በኩል ሊደርሳቸው እንደሚገባ ማርክ ፋርሜነር አደራ ብለዋል። የዕርዳታ አሰጣጥ በዘዴ መከናወን እንዳለበት እና ዕርዳታ ለጋሾች ከተለያዩ የአካባቢ አስተዳደሮች፣ በሀገሪቱ ውስጥ ካሉ ብሔረሰቦች አስተዳደሮች እና ከአካባቢው የሲቪል ማኅበረሰብ አውታረ መረቦች አስተባባሪዎች ጋር መሥራት አለባቸው” ብለዋል።

ቤተ ክርስቲያን ምን ማድረግ ትችላለች

ብዙውን ጊዜ በቁምስናዎች አማካይነት ከነዋሪው ማኅበረሰብ ጋር በቅርበት የምትሠራው ቤተ ክርስቲያን ለመሬት መንቀጥቀጡ ምላሽ ወሳኝ ሚና መጫወት እንደምትችል ማርክ ፋርማን አስረድተው፥ ሠራዊቱ በእንቅስቃሴያቸው ላይ ያን ያህል ጥብቅ ገደቦችን ባለማስቀመጡ ለዓለም አቀፍ የረድኤት ኤጀንሲዎች ሊታገዱ የሚችሉ ቦታዎችን የመድረስ አቅም እንዳላቸው እና ትንንሽ ማኅበረሰቦችን መሠረት ያደረጉ ዕርዳታዎችን በሚያስፈልጉ ቦታዎች በማድረስ ረገድ ውጤታማ ሊሆኑ እንደሚችሉ አስረድተዋል።

የቀውሱን ክብደት ለማወቅ መሞከር

አሁን እየተከሰተ ያለው የአደጋው መጠን በወታደራዊ አገዛዝ እና በጎሳ ግጭቶች ተለይቶ የሚታወቀው የማይናማር የፖለቲካ ሁኔታ ለዓለም አቀፍ የዕርዳታ ጥረቶች ከፍተኛ ፈተናዎችን ፈጥሯል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመሬት መንቀጥቀጥ የተጎዱትን በጸሎት በማስታወስ የተቻላቸውን ሁሉ እንደሚያደርጉ፣ የነፍስ አድን ሠራተኞችም በተቻለ መጠን የብዙዎችን ሕይወት ለማዳን እንደሚያግዙ ገልጸዋል።

ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የአደጋውን ሁኔታ በቅርበት የሚከታተለው ሲሆን፥ ውጤታማ መፍትሄዎች እና ጠንካራ የሀገር ውስጥ መዋቅሮች ዕርዳታው የተጎዱት ሰዎችን እንዲደርስ፣ የጉዳቱን መጠን ለመገደብ እና በአሰቃቂ አደጋ እጅግ የተጎዱትን ለማዳን እንደሚያስችል ተስፋ መኖሩ ታውቋል።

 

29 Mar 2025, 16:06