በዓለም የውሃ ቀን የተባበሩት መንግስታት የበረዶ ግግርን ለመጠበቅ የሚያስችል እርምጃ እንዲወሰድ ጠየቀ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
መጋቢት 13 ቀን 2017 ዓ.ም. የዓለም የውሃ ቀን የተከበረ ሲሆን፥ ይህ በዓል በየዓመቱ የሚከበረው ንፁህ ውሃ ለምድራችን ያለውን ጠቀሜታ ግንዛቤ ለማስጨበጥ እና የውሃ ሃብትን በዘላቂነት ለመጠበቅ እገዛ ለማድረግ እንደሆነ ተገልጿል።
ከዚህም ባለፈ ቀኑ የሚከበረው የውሃ ቀውስ ግንዛቤን ለማዳበር እና የውሃ እና የአካባቢ ጽዳትን ለሁሉም ማረጋገጥ የሚለውን እቅድ ለማሳካት እና ለመደገፍ በማለም እንደሆነም ተገልጿል።
2.2 ቢሊዮን ሰዎች ንፁህ እና ደህንነቱ የተጠበቀ የመጠጥ ውሃ አያገኙም
እ.አ.አ. በ 1992 ዓ.ም. በሪዮ ዴጄኔሮ በተካሄደው የዓለም የአካባቢ እና ልማት ጉባኤ ላይ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የተመሰረተው ይህ ዓለም አቀፋዊ ክስተት በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የዓለም ሀገራትን የሚያጠቃውን ከባድ የውሃ ችግር ለማጉላት እና ግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ ሆኖ ያገለግላል። በዓሉ በአውሮፓዊያኑ 2030 ለሁሉም ሰው የውሃ አቅርቦትን እና የአከባቢ ንፅህናን ለማረጋገጥ ከታቀደው ዘላቂ የልማት ግብ SDG - 6 ጋር በቅርበት የተሳሰረ እንደሆነ የተነገረ ሲሆን፥ በአሁኑ ወቅት ዓለም ላይ 2.2 ቢሊዮን የሚጠጉ ሰዎች ንጹህና ደህንነቱ የተጠበቀ የመጠጥ ውሃ እንደማያገኙ መረጃዎች ያመላክታሉ።
ከዚህ በፊት ታይቶ በማይታወቅ ፍጥነት የበረዶ ግግር እየቀለጡ ይገኛሉ
ለዘንድሮው የዓለም የውሃ ቀን የተመረጠው መሪ ሃሳብ የበረዶ ግግር ጥበቃን አስፈላጊነት የሚያጎላ ሲሆን፥ ይህም 70 በመቶውን የዓለም ንጹህ ውሃ የሚይዘውን የበረዶ ግግርን እና ንጣፍን ለመጠበቅ አስፈላጊ መሆኑን እንደሚያሳይ፥ ነገር ግን ይህ የበረዶ ግግር በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ታይቶ በማይታወቅ ፍጥነት በመቅለጥ የውሃ ደህንነትን፣ ስነ-ምህዳሮችን እና በዓለም ላይ ያለውን የአኗኗር ሁኔታ አደጋ ላይ እየጣለ እንደሚገኝ ተገልጿል።
እ.አ.አ. ከ 1975 ዓ.ም. ጀምሮ በዓለም ዙሪያ ያሉ የበረዶ ግግሮች (ከግሪንላንድ እና ከአንታርክቲክ የበረዶ ግግር በስተቀር) ከ9,000 ቢሊዮን ቶን በላይ በረዶ ወይም በንፅፅር በአጠቃላይ የጀርመን ቆዳ ስፋት ላይ 25 ሜትር ውፍረት ያለው የበረዶ ንጣፍ የሚፈጥር መጠን ያለው የበረዶ ግግር መቅለጡ የተነገረ ሲሆን፥ የዓለም የሚቲዎሮሎጂ ድርጅት (WMO) እና የዓለም የበረዶ ግግር ክትትል አገልግሎት (WGMS) እንደገለጹት ካለፉት ስድስት ዓመታት ውስጥ በአምስቱ በጣም ፈጣን የሆነ የበረዶ መቅለጥ መመዝገቡን ይፋ አድርገዋል።
እ.አ.አ. ከ 2022 እስከ 2024 ባለው የሦስት ዓመታት ጊዜ ውስጥ እስካሁን ድረስ ከተመዘገቡት በጣም ከፍተኛ የበረዶ ግግር እንደቀለጠ መረጃዎች ያሳዩ ሲሆን፥ በ 2024 ዓ.ም. በሶስተኛው ተከታታይ ዓመታት በ 19 ክትትል በሚደረግባቸው ክልሎች ከፍተኛ የተጣራ የበረዶ ግግር መቅለጥ የተከሰተበት ዓመት ሆኖ መመዝገቡ ተገልጿል። ልክ እንደ ካናዳ አርክቲክ ያሉ አንዳንድ አካባቢዎች መጠነኛ የመቅለጥ አዝማሚያዎች የታዩባቸው አከባቢዎች ሲሆኑ፥ ነገር ግን እንደ ስካንዲኔቪያ እና ሰሜን እስያ ያሉ የበረዶ ግግሮች በከፍተኛ ሁኔታ በመቅለጥ ሪከርድ አስመዝግበዋል።
እንደ መካከለኛው አውሮፓ ያሉ አንዳንድ ክልሎች 40 በመቶ የሚጠጋ የበረዶ ግግር ቀልጦ የጠፋ ሲሆን፥ ይህም የአየር ንብረት ለውጥ ተጽእኖዎች ምን ያህል ያልተመጣጠነ እንደሆነ ያሳያሉ ተብሏል።
በብዙ ክልሎች በአንድ ወቅት “ዘላለማዊ የበረዶ ክምችት” አላቸው ተብለው የሚታሰቡ የበረዶ ግግሮች፥ በአሁኑ ወቅት ከ21ኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻ በፊት ሊጠፉ ይችላሉ ተብሎ ግምት ተሰጥቷቸዋል።
የበረዶ ግግር መቅለጥ በአከባቢያዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ እና ጂኦፖለቲካዊ ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖ
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ለዘንድሮው የዓለም የውሃ ቀን ባስተላለፉት መልዕክት ላይ እንዳብራሩት የበረዶ ግግር መጥፋት የአካባቢያዊ ስጋት ብቻ ሳይሆን ሰፊ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ እና ጂኦፖለቲካዊ መዘዞች እንዳሉት ገልጸዋል።
የእነዚህ የበረዶ ክምችቶች መሟጠጥ በበረዶ ግግር ውሃ ላይ ተማምነው ለሚኖሩ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች ላይ፣ በተለይ በጣም ሞቃታማ እና ደረቅ ወቅቶች ላይ የውሃ አቅርቦት ስጋት እንደሚያሳድር የሚታወቅ ሲሆን፥ በአጭር ጊዜ ውስጥ እየጨመረ የመጣው የበረዶ ግግር መቅለጥ ግብርና እና ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ያላቸውን ድርቅ እና የመሬት መንሸራተትን የመሳሰሉ ከባድ የተፈጥሮ አደጋዎችን እንደሚያስፋፉም ጭምር ተገልጿል።
የባህር ከፍታ መጨመር
የበረዶ ግግር መጥፋት ከሚያስከትላቸው አስደንጋጭ መዘዞች አንዱ ለባህር ከፍታ መጨመር ያለው አስተዋፅኦ ሲሆን ይህም የአየር ንብረት ለውጥን በከፍተኛ ሁኔታ ይጨምራል ተብሏል። የበረዶ መቅለጥ የውቅያኖስ ሙቀት መጨመርን ተከትሎ ለባህር ከፍታ መጨመር ሁለተኛው ትልቁ አስተዋፅዖ እንደሆነ የሚነገር ሲሆን፥ አንዳንድ ጥናቶች እንደሚያሳዩት እንደ አውሮፓዊያኑ ከ 2000 እስከ 2023 ዓ.ም. ባለው ጊዜ ውስጥ 6,542 ቢሊዮን ቶን የበረዶ ግግር እንደቀለጠ እና በዚህም ምክንያት የባህር ጠለል በ 18 ሚሊ ሜትር ከፍ ማለቱ የተዘገበ ሲሆን፥ ይህ አሃዝ እዚህ ግባ የማይባል ቢመስልም እያንዳንዱ ተጨማሪ ሚሊ ሜትር በከተሞች እና በገጠር የሚኖሩ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ለጎርፍ አደጋ እንዲሁም ለመጠጥ ውሃ እና ለግብርና የምንጠቀመውን ውሃ ጨዋማ እንዲሆን ያደርጋል ተብሏል።
በዝቅተኛ ደረጃ ላይ ያሉ ማህበረሰቦች እና በርካታ ሃገራት የህልውና ስጋቶች እያጋጠሟቸው ሲሆን ለውሃ እና መሬት ይዞታ የሚደረጉ የግጭት ውጥረቶችን እያባባሰ እንደሆነም ተገልጿል።
ለተግባር የተደረገ ጥሪ
እነዚህ ችግሮች የአየር ንብረት እርምጃውን ይበልጥ አስቸኳይ ያደርገዋል ያሉት ጉቴሬዝ፥ ሁሉም ሃገራት ጠንካራ ብሄራዊ የአየር ንብረት የድርጊት እቅዶችን እንዲያቀርቡ እና ለአየር ንብረት ጥበቃ እና መቋቋም የሚደረገውን የገንዘብ ድጋፍ እንዲጨምሩ በመጠቆም፥ “የበረዶ ግግር እየቀነሰ ሊሆን ይችላል፥ ነገር ግን እኛ በኃላፊነት የምናደርገውን ነገር መቀነስ አንችልም” በማለት ሁሉም የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ አሳስበዋል።