ፈልግ

ጆዜፍ ኡልማ እና ባለቤቱ ቪክቶሪያ ከሰባት ልጆቻቸውን ጋር ጆዜፍ ኡልማ እና ባለቤቱ ቪክቶሪያ ከሰባት ልጆቻቸውን ጋር   (ANSA)

ፖላንድ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት አይሁዳዊያንን ለመታደግ ብለው ሕይወታቸውን ያጡትን ዜጎቿን አስታወሰች

በፖላንድ ሉብሊን ከተማ የሚገኘው የዮሃንስ ጳውሎስ 2ኛ የካቶሊክ ዩኒቨርስቲ (KUL) በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት አይሁዶችን ከሞት የታደጉ ፖላንዳዊያን መታሰቢያ ብሄራዊ ቀን ላይ የሌሎች ሰዎችን ህይወት ለማትረፍ ብለው የራሳቸውን ሕይወት ያጡትን ሁሉ ለማሰብ በሚል የመታሰቢያ መስዋእተ ቅዳሴ እና ጋዜጣዊ መግለጫ አዘጋጅቷል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

እ.አ.አ. በ1944 ዓ.ም. ለአይሁዶች ጥገኝነት በመስጠታቸው እና ከጥቃት ለመታደግ በቤታቸው ሸሽገው አስቀምጠው በመገኘታቸው የተነሳ በናዚዎች የተገደሉትን ስምንት የኡልማ ቤተሰብ አባላት ማለትም ጆዜፍ ኡልማ፣ ነፍሰ ጡር የነበረችው ባለቤቱ ዊክቶሪያ እና ስድስት ህፃናት ልጆቻቸውን ለማስታወስ መጋቢት 15 ቀን 2017 ዓ.ም. የሉብሊን ዮሃንስ ጳውሎስ 2ኛ የካቶሊክ ዩኒቨርስቲ ልዩ የመታሰቢያ ቀን ያዘጋጀ ሲሆን፥ በጀርመኖች ከተገደሉት ፖላንዳዊያን በተጨማሪ በኡልማ ቤተሰብ መኖሪያ ቤት ውስጥ ተጠልለው የነበሩ ስምንት አይሁዳዊያን ጎሽዳ ግሩንፌልድ፣ ሊያ ዲነር እና ሴት ልጇ እንዲሁም ሳውል ጎልድማን እና አራት ወንድ ልጆቹ በጀርመኖች ተገድለዋል።

እንደ አውሮፓዊያኑ የቀን አቆጣጠር ከ 2018 ዓ.ም. ጀምሮ ፖላንድ መጋቢት 24ን በጀርመን ወረራ ወቅት አይሁዶችን የታደጉ ፖላንዳዊያንን ለማሰብ ብሔራዊ የመታሰቢያ ቀን አድርጋ ማወጇ ይታወሳል።

እ.አ.አ. መጋቢት 24 ቀን 1941 ዓ.ም. የፀረ-አይሁዶች የጥላቻ ምልክት የሆነው ‘የሉብሊን ጌቶ’ ተብሎ የሚጠራው የአይሁዶች ማቆያ መንደር በመመስረቱ በታሪክ ውስጥ ሌላ የጨለማ ምዕራፍ የተፈጠረ ሲሆን፥ ይህ መንደር በጀርመን ቁጥጥር ሥር በነበረችው ፖላንድ የጠቅላይ መንግስት ግዛት በሆነችው ሉብሊን ከተማ በናዚ ጀርመን የተፈጠረ የሁለተኛው የዓለም ጦርነት አስከፊ ቦታ እንደነበር፣ ብሎም በመንደሩ ውስጥ በአብዛኛው የፖላንድ አይሁዶች እንደነበሩ መረጃዎች ያሳያሉ።

“በአንድ ወቅት የተለያዩ ባህሎችን እና ሃይማኖቶችን የተቀበለች፣ የተለያየ ዘር ያላቸው ዜጎችን ያቀፈች ከተማ ፈራርሳለች፥ አንድ ባህል፣ አንድ ሀይማኖት በግዳጅ ተወግዶ ከአጥር ጀርባ ተዘግቶበታል” በማለት የሉብሊን ዮሃንስ ጳውሎስ ሁለተኛ የካቶሊክ ዩኒቨርሲቲ ዳይሬክተር አባ ሚሮስሎው ካሊኖስኪ በወቅቱ ሉብሊን ላይ ስለደረሰው ሁኔታ ገልጸዋል።

የጀግንነት እና የቁርጠኝነት ተግባራት
የሉብሊን ይፋዊ መታሰቢያ ሥነ ስርዓቶች ከመካሄዳቸው በፊት ቀኑን በማስመልከት ሰኞ ዕለት የወጣው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የአካባቢው እና የክልል ባለስልጣናት እንዲሁም ከብሔራዊ የመታሰቢያ ተቋም የሉብሊን ቅርንጫፍ ተወካዮች የተገኙ ሲሆን፥ የዕለቱ ዝግጅቶች በሉብሊን ካቴድራል በተካሄደ መስዋዕተ ቅዳሴ ተጀምሮ፣ በመቀጠልም በኡልማ ቤተሰብ ሥም የተዘጋጀ አውደ ርዕይ ከተከፈተ በኋላ፥ በመጨረሻም በስሎኒም ከተማ አቅራቢያ አይሁዳውያንን በማስጠለሏ የተገደለችው በእህት ማርታ ዎሎውስካ መኖሪያ ቤት ውስጥ የመታሰቢያ አበባዎች ተቀምጠዋል።

ብሔራዊ የመታሰቢያ ቀንን በመጥቀስ አባ ካሊኖቭስኪ አጽንዖት ሰጥተው እንደተናገሩት ‘ይህ ቀን ‘የቅድስና ሕይወት’ ተብሎ ከምከበረው ዕለት ቀደም ብሎ በመከበሩ ልዩ ትርጉም አለው’ ያሉ ሲሆን፥ በዚህም እራሳቸውም ሆኑ የሚወዷቸው ሰዎች የሞት ቅጣት እንደሚደርስባቸው ሙሉ በሙሉ እያወቁ በታላቅ ድፍረት እና ቁርጠኝነት ስደት የደረሰባቸውን አይሁዶች ለመርዳት ሕይወታቸውን አደጋ ላይ የጣሉት ፖላንዳዊያን እንደሚከበሩበት በመግለጽ፥ “የእነዚህ የተደበቁ ጻድቃን ጀግኖች ተምሳሌትነት ሌሎች የእኛን እርዳታ ሲፈልጉ በድፍረት ለመርዳት ወደ ኋላ እንዳንል ያበረታታናል” ብለዋል።

'በሌላ ሃገራት ዘንድ ብዙም አይታወቁም'
በፖላንድ በሰፊው የሚታወቀው የኡልማ ቤተሰብ ታሪክ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በሌሎች ሃገራት ብዙም እንደማይታወቁ የተገለጸ ሲሆን፥ ከሉብሊን የካቶሊክ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር የተዘጋጀው እና በተባባሪ ደራሲ ማኑዌላ ቱሊ “የኡለማ ቤተሰብ ታሪክ፣ አይሁዶችን የረዱ ሰማዕታት፡ ሕፃናትንም ጭምር ገድለዋል” በሚል ርዕስ በወቅቱ ስለተደረገው ነገር የሚተርከው መጽሐፍ ስለ እውነታው በጥቂቱ ግንዛቤ ማስጨበጡ ተነግሯል።

“አይሁዳዊያንን ስለታደጉ ፖላንዳውያን በሌሎች ሃገራት የተነገረው በጣም ጥቂት ነው” ያለው ደራሲ ጋዜጠኛው፥ በማከልም “ከአባ ፓዌል ራይቴል-አንድሪያኒክ ጋር በመሆን የኡልማን ታሪክ ለጣሊያን ህዝብ አስተዋውቀናል፥ አሁን በሚያስደንቅ ሁኔታ ታሪካቸው በስፋት ታውቋል፥ አንድን ሀገር በሙሉ ቀይረናል ማለት ይቻላል” ሲል ተናግሯል።

ጀግና የሆኑ ሴቶች
በሉብሊን ካቶሊክ ዩኒቨርሲቲ የቤተክርስቲያን ታሪክ ጥናት ማዕከል አባል የሆኑት እህት ሞኒካ ኩፕዜውስካ በበኩላቸው “ገዳማዊያት እህቶች በጦርነት ወቅት ስለሚያደርጉት እንቅስቃሴ እና ለአይሁዳዊያን ልጆች እና ቤተሰቦች በሚያደርጉት እርዳታ ላይ ብዙ ጥናቶች ታትመዋል” ያሉ ሲሆን፥ ሆኖም እንደ እህት ማርታ ዎሎቭስካ ያሉ ተጨባጭ አኃዛዊ መረጃዎች ብዙም እንደማይታወቁ ገልጸው፥ በታሪካዊ ሁነቶች ኮሚሽን ውስጥ በመነኮሳት ቡድን የተካሄደው ጥናት እያንዳንዷን እህት በስም ለመለየት ያለመ እንደሆነ እና በዚህም 2,345 እህቶች አይሁዶችን የመርዳት ሥራ ይሰሩ እንደነበር ለማወቅ ተችሏል ብለዋል።

እህት ሞኒካ አክለውም “አይሁዳውያንን መታደግ በሌሎች የአውሮፓ አገሮች በጣም ቀላል እንደነበር፥ በፖላንድ ግን እንዲህ ዓይነቱ ድርጊት በሞት ያስቀጣል” በማለት ተግባሩ ምን ያክል ከባድ እንደነበር ካስረዱ በኋላ፥ እነዚህ ደፋር እና ጀግና ሴቶች ፖላንድ ውስጥ ከሚገኙ በርካታ ጉባኤዎች የተውጣጡ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

ካህናት አይሁዶችን መታደጋቸውን የተሰጡ ልዩ ምስክርነቶች
በዩኒቨርሲቲው ውስጥ በሚገኘው እና በአብርሃም ጄ.ሄሽል የተሰየመው የካቶሊክ-አይሁዶች ግንኙነት ማዕከል በሚሰራቸው ሥራዎች በኩል የሉብሊን የካቶሊክ ዩኒቨርሲቲ የአይሁድ ህዝብን ለማዳን የተፈጸመውን ተግባር በፖላንድ ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና እንዲያገኝ እየሰራ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፥ ከእነዚህ ጥረቶች አንዱ ስለ ኡልማ ቤተሰብ የተፃፈው መጽሐፍ አንዱ ሲሆን፥ በተጨማሪም ጠበቃ እና የታሪክ ምሁር በሆኑት ራይዛርድ ቲንዶርፍ “ፖላንዳዊያን የካቶሊክ ካህናት በጦርነቱ ወቅት አይሁዶችን መታደጋቸው” በሚል ርዕስ በእንግሊዘኛ የተዘጋጀው ባለ ሁለት ጥራዝ መጽሃፍ እንደሚገኝበት እና መጽሐፉ በዋነኛነት በፖላንድ ሆሎ-ኮስት ጊዜ በገዳማዊያት እህቶች እና ገዳማዊያን አባቶች እገዛ ከሞት የተረፉት አይሁዶች የሰጡትን ምስክርነቶች በብዛት እንዳካተተ የተጠቆመ ሲሆን፥ ይሄንን ባለ 1,200 ገፅ መጽሃፍ በድህረ ገጽ (https://tiny.pl/s8xxn5vc) ላይ በነፃ ማግኘት እንደሚቻልም ተገልጿል።
 

25 Mar 2025, 13:58