በኢትዮጵያ ትግራይ ክልል ውስጥ እያገረሸ ያለው ውጥረት አዲስ ግጭትን ሊቀሰቅስ ይችላል የሚል ስጋት ማሳደሩ ተነገረ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
በ 2014 ዓ.ም. በደቡብ አፍሪካ የኢትዮጵያ መንግስት እና ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) የተፈራረሙት የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት በኢትዮጵያ ትግራይ ክልል ለሁለት ዓመታት ሲካሄድ የቆየውን የእርስ በርስ ጦርነት ያስቆመ ቢሆንም፥ አሁንም ድረስ በአከባቢው የሚታየው ፖለቲካዊ አለመረጋጋት ቀጠናውን የሰላም መደፍረስ ስጋት ላይ መጣሉ እየተነገረ ይገኛል።
በትግራይ የሽግግር አስተዳደሩ አመራር ውስጥ ያለው ውጥረት እየሰፋ መጥቷል
ምንም እንኳን ከስምምነቱ መፈረም በኋላ የተኩስ አቁም ተደርጎ ጦርነቱ ቢቆምም፥ የስምምነቱ አካል የሆኑ ሌሎች ጉዳዮች ተፈጻሚነት መዘግየቶች እንደገጠሙት በሁለቱም ወገን ሲገለጽ የቆየ ሲሆን፥ ይህም በመሃከላቸውም ውጥረቱን እያሰፋ መሄዱ ይነገራል።
ካለፈው ዓመት ጀምሮ እየተባባሰ የመጣው የሰሞኑ ውዝግብ መንስኤ በራሱ በህወሓት ውስጥ ያለው የስልጣን ሽኩቻ ሲሆን፥ በዚህም ለረዥም ጊዜያት ያክል በክልሉ በመሪነት ሥፍራ በቆዩት አቶ ደብረፂዮን ገብረሚካኤልን እና የቀድሞ ምክትላቸው፣ የአሁኑ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ሃላፊ ከሆኑት አቶ ጌታቸው ረዳ መካከል ሲካሄድ የነበረው ግጭት ወደ ለየለት ጦርነት እንዳይሸጋገር ያሰጋል ተብሏል።
የሁለቱ አመራሮች አለመግባባት በዋናነት ያተኮረው ትግራይን ወደ ኢትዮጵያ ፌዴራላዊ አወቃቀር ለማዋሃድ የተቀየሰውን የጦርነት ማቆም ስምምነት (COHA) አፈፃፀም ላይ እንደሆነ ይነገራል። አቶ ደብረጽዮን ስምምነቱ አዝጋሚ እና ውጤታማ አይደለም በማለት አቶ ጌታቸውን የሚከሱ ሲሆን፥ ከዚህም ባለፈ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር እንዲፈርስ ብቻ ሳይሆን የአቶ ጌታቸውን ስልጣን ህጋዊነት እንደማይቀበሉ ይገልፃሉ።
ባለ 12 አንቀፁ የፕሪቶሪያው ስምምነት ጦርነቱን ከማስቆም ባለፈ የዜጎች ደኅንነት እንዲረጋገጥ፣ መልሶ ግንባታ እንዲካሄድ፣ ተጠያቂነት እንዲሰፍን እና በጦርነት እና በረሃብ የተጎዱ አካባቢዎች እንዲያገግሙ ያለመ ነው።
በመጋቢት ወር መጀመሪያ ላይ ለደብረፂዮን ታማኝ የሆኑት የተወሰኑ የትግራይ መከላከያ ሰራዊት አባላት በትግራይ የሚገኙ ቁልፍ ቦታዎችን ጨምሮ በመቀሌ የሚገኘውን የክልሉን ራዲዮ ጣቢያ እና ከንቲባ ጽ/ቤትን፣ እንዲሁም በኤርትራ ድንበር ላይ የሚገኙ ከተሞችን መቆጣጠራቸው ውጥረቱ ከፍተኛ ደረጃ ላይ እንዳደረሰው ይነገራል።
አቶ ጌታቸው በምላሹ ሶስት የሕወሓት አዛዦችን ከስራ በማገድ እና የፌደራል ጣልቃ ገብነት እንዲፈቀድላቸው በመጠየቅ ወሳኝ እርምጃ ወስደዋል። የእነዚህ ሁኔታዎች ድምር ውጤት ሰሜን ኢትዮጵያ እንደገና ወደ ከፍተኛ ጦርነት ምናልባትም ኤርትራ በቀጥታ ልትሳተፍ የምትችልበት ጦርነት ሊነሳ ይችላል የሚል ስጋትን ጨምሯል።
ብጹእ አቡነ ተስፋሥላሴ መድህን ሌላ ጦርነት አስከፊ መዘዝ ይኖረዋል ማለታቸው
በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የዓዲግራት ሃገረ ስብከት ጳጳስ የሆኑት ብጹእ አቡነ ተስፋሥላሴ መድህን ከፊደስ የዜና ኤጀንሲ ጋር ባደረጉት ቆይታ በእነዚህ ጉዳዮች ላይ ያላቸውን ስጋት በመግለጽ፥ ሌላ ጦርነት ከፍተኛ ስቃይ በደረሰበት ህዝብ ላይ የሚያመጣውን አስከፊ መዘዝ ገልጸዋል።
ጳጳሱ በትግራይ ክልል ያለውን አስከፊ ሰብዓዊ ሁኔታ ጠቁመው፥ በዚህ ላይ ደግሞ የዩ.ኤስ.ኤ.አይ.ዲ የገንዘብ ድጋፍ በድንገት መቆም ሁኔታውን እያባባሰው እንደሆነ ገልጸዋል።
የዩ.ኤስ.ኤ.አይ.ዲ(USAID) የገንዘብ ድጋፍ በድንገት በመቋረጡ የሰብዓዊ ቀውሱ ይበልጥ ተባብሷል
በዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ውሳኔ የአሜሪካ የረድኤት ድርጅት በሆነው የዩ.ኤስ.ኤ.አይ.ዲ በኩል ሲደረግ የነበረው ድጋፍ መቋረጡ በመንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ የሃይማኖት ድርጅቶች እና የመንግስት ኤጀንሲዎች የሚመሩ ወሳኝ የእርዳታ ፕሮግራሞችን ክፉኛ ጎድቷል።
በኢትዮጵያ የአስቸኳይ ጊዜ የምግብ ዕርዳታ ከሚሰጡ ድርጅቶች መካከል አንዱ የሆነው የዩናይትድ ስቴትስ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ዓለም አቀፍ የሰብአዊ እርዳታ ተቋም የሆነው የካቶሊክ የእርዳታ አገልግሎት (CRS) በአሁኑ ወቅት ውስን የሆኑ ትንንሽ ድጋፎችን ከማድረግ በስተቀር ሙሉ በሙሉ የእርዳታ ሥራውን አቋርጧል።
እነዚህን ሰብዓዊ ፍላጎቶች ለመቅረፍ የሚያስችል አማራጭ ስልት አለመኖሩ ቀውሱን የበለጠ ያባባሰው ሲሆን፥ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ለችግር የተጋለጡ ዜጎች ድጋፍ እንደተቋረጠባቸው እና በዚህም ምክንያት ከአጠቃላይ የክልሉ ህዝብ ብዛት 15 በመቶ የሚሆነው ከአከባቢው ተፈናቅሏል።
ምንም እንኳን ከባድ ችግር ቢኖርም የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ለተጎዱት ሰዎች ቁሳዊ እርዳታን እና መንፈሳዊ ድጋፍን በመስጠት ወሳኝ ሚና መጫወቷን አጠናክራ የቀጠለች ሲሆን፥ ብጹእ አቡነ ተስፋሥላሴ እንደተናገሩት፥ “እንደ ቤተ ክርስቲያን ወደፊት ለመራመድ፣ ለሰዎች ተስፋ ለመስጠት እና ለእነሱ የተስፋ ምልክት ለመሆን እየሞከርን እንገኛለን” ካሉ በኋላ፥ “ከጎናቸው ለመቆም እና ጦርነቱ ካስከተለው ጉዳት እንዲያገግሙ ለመርዳት እንጥራለን” ብለዋል።