አስከፊው የሱዳን ግጭት ሁለት ዓመት ሊሞላው እንደሆነ ተነገረ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
ባለፈው ሳምንት መጨረሻ በሱዳን ምዕራባዊ ዳርፉር ክልል በደረሰ ጥቃት ከ20 ያላነሱ ህጻናት እና የህክምና ቡድን ጨምሮ ከ100 በላይ ንፁሀን ዜጎች ህይወታቸውን አጥተዋል።
በ 2015 ዓ.ም. ሚያዚያ ወር ላይ የተጀመረው የሱዳን ግጭት በሱዳን ጦር ሃይሎች (SFA) እና በፈጣን የድጋፍ ሰጪ ሃይሎች (RSF) መካከል በተፈጠረ ጭካኔ የተሞላበት የስልጣን ሽኩቻ ምክንያት እንደሆነ የሚታወቅ ሲሆን፥ የእርስ በርስ ጦርነቱ ከተነሳበት ጊዜ አንስቶ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች መፈናቀል፣ ለሺዎች ሞት እና ከባድ ሰብዓዊ ቀውስን አስከትሏል፥ ብሎም በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች ለከፍተኛ ምግብ እጦት ተዳርገዋል።
ሁለቱንም ወገኖች ለማደራደር የተደረጉ የሽምግልና ጥረቶች በአብዛኛው ውጤታማ እንዳልሆኑ የሚታወቅ ሲሆን፥ አርብ እለት የፈጣን ድጋፍ ሰጪ ሃይሎች (RSF) ከተባባሪ ሚሊሻዎች ጋር በመሆን በዳርፉር በረሃብ በተጠቁ የተፈናቃይ ካምፖች ላይ ለሁለት ቀናት የዘለቀ አሰቃቂ ጥቃት በመሰንዘር ከ100 በላይ ሰዎች መሞታቸውን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ባለስልጣን ተናግረዋል።
በዛምዛም እና በአቡ ሾሩክ ካምፖች እንዲሁም በአቅራቢያው በምትገኘው የሰሜን ዳርፉር ግዛት ዋና ከተማ በሆነችው ኤል-ፋሸር ከተማ ላይ ኢላማ ተደርጎ በተፈጸመ ጥቃት ከተገደሉት መካከል 20 ህጻናት እና ዘጠኝ የእርዳታ ሰራተኞች እንደሚገኙበት ተገልጿል።
ባለፈው ወር የመንግስታቱ ድርጅት የሰብአዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ፅህፈት ቤት በሱዳን ያለውን ሰብአዊ ቀውስ ለመቅረፍ አፋጣኝ እርምጃ እንዲወሰድ አሳስቦ እንደነበረ ይታወሳል።
ወደ 24.6 ሚሊዮን የሚጠጋው ከግማሽ በላይ የሚሆነው የሀገሪቱ ህዝብ በከፍተኛ ረሃብ እየተሰቃየ የሚገኝ ሲሆን፥ ከዚህም በተጨማሪ በአሁኑ ወቅት ከ12 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ከቤት ንብረታቸው እንደተፈናቀሉ እና 3.4 ሚሊዮን የሚሆኑት ደግሞ ድንበር ተሻግረው ለመሰደድ ተገደዋል።
በሁለቱ ወገኖች መካከል እየተካሄደ ባለው ግጭት ምክንያት የሃገሪቱ ጤና አገልግሎት እንዲወድቅ፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ህጻናት ከትምህርት ገበታቸው ውጪ እንዲሆኑ እና ጾታዊ ጥቃት እንዲስፋፋ አድርጓል።
በሱዳን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ እርዳታ አስተባባሪ የሆኑት ክሌመንት ንክዌታ ሳላሚ በሃገሪቱ እየታየ ያለው የሰብአዊ ሁኔታ አስከፊ መሆኑን ገልጸው፥ “ወደ ግጭት ከገባን ሁለት ዓመት ሊሆነን ነው፥ ይሄንን መልዕክት ብዙ ጊዜ አስተላልፈናል፥ ለተቸገሩት ሁሉን አቀፍ ሰብዓዊ እርዳታ መስጠት እንደምንችል ተስፋ አድርገን ነበር” ብለዋል።
የተባበሩት መንግስታት ወደ ሁሉም ችግሩ የተከሰተባቸው የመዳረሻ ቦታዎች ለመድረስ ምቹ መንገድ እንዳልነበረው ያስታወሱት ሃላፊዋ፣ በመጨረሻም፥ “ሁሉንም ዘዴዎች በመጠቀም ያለንን ሃብቶች በተቻለ ፍጥነት አውጥተን ተግባር ላይ ለማዋል የተቻለንን ሁሉ እየሞከርን እንገኛለን” በማለት አጠቃለዋል።