ፈልግ

በሮም የተካሄደው ጉባኤ በሮም የተካሄደው ጉባኤ  

ሃይማኖታዊ እና ማህበራዊ ትስስርን ለማዳበር ያለመ ጉባኤ በሮም መካሄዱ ተነገረ

በአየር ንብረት ፍትሕ፣ በማህበራዊ ትስስር እና በሃይማኖት ተቋማት መካከል ስላለው ግንኙነቶች ዙሪያ ውይይት ለማድረግ በሮም የሁለት ቀናት ጉባኤ የተካሄደ ሲሆን፥ በጉባኤ ላይ ብጹአን ካርዲናሎች፣ አምባሳደሮች እና የሉተራን ብጹአን ጳጳሳት እንደተገኙ ተነግሯል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

ሃይማኖታዊ ተቋማት ማህበራዊ ትስስርን እና የአየር ንብረትን ፍትህን ለማስፈን አብረው ለመስራት የሚቻልባቸውን መንገዶች ለመፈለግ ‘የጋራ አድማስ - በአውሮፓ የሃይማኖት ተቋማት መካከል ማህበራዊ ትስስርን እና የአየር ንብረት ፍትህን መፈለግ’ በሚል ርዕስ ሮም በሚገኘው ጳጳሳዊ አንቶኒየም ዩንቨርስቲ የስብሰባ ማእከል ውስጥ ከመጋቢት 30 እስከ ሚያዚያ 1 ቀን 2017 ዓ.ም. ድረስ ውይይት እንደተካሄደ ተገልጿል።

አዲስ የተሾሙት የቅድስት መንበር የሃይማኖት ተቋማት ውይይት ጽህፈት ቤት ሃላፊ የሆኑት ብፁዕ ካርዲናል ጆርጅ ኮቫካድ በጉባኤው ላይ ቀድመው ንግግር ያደረጉ ሲሆን፥ ብጹእነታቸው በንግግራቸው ወቅት የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት በነዲክቶስ 16ኛን አስተያየት በማስታወስ፥ “ምንም እንኳን ግሎባላይዜሽን ‘ጎረቤታሞች’ ቢያደርገንም፣ ወንድማማቾች ግን አያደርገንም” ብለዋል።

‘በአምላክ ላይ ማመን ብቻውን የፕላኔታችንንም ሆነ የሌሎች ሰዎችን ፍላጎት በትኩረት ለመከታተል በቂ አይደለም’ በማለት የተናገሩት ካርዲናል ኮቫካድ፥ ከዚህም ይልቅ የሚያስፈልገው መንፈሳዊነት እና ‘በቴክኖሎጂ መጥቀው የሄዱ ባለሙያዎች አካሄድን’ መቋቋም የሚችል የህይወት ዘይቤ ያስፈልገናል ሲሉ በአጽንዖት ተናግረዋል።

ከእሳቸው በመቀጠል ንግግር ያደረጉት የዓለም አቀፍ የውይይት ማዕከል ተጠባባቂ ዋና ፀሀፊ የሆኑት አምባሳደር አንቶኒዮ ዴ አልሜዳ-ሪቤሮ ሲሆኑ፥ በሃይማኖታዊና ዓለማዊ ተቋማት መካከል ያለውን ትብብር አስፈላጊነትን አሳስበዋል።

አምባሳደር አልሜዳ-ሪቤሮ እንደተናገሩት ሃይማኖቶች ማህበራዊ ትስስርን እና የዘመናት ጥበብን ሲሰጡ፥ ፖሊሲ አውጪዎች በበኩላቸው ግንዛቤያቸውን ወደ ገንቢ የፖሊሲ ፕሮፖዛል ለመቀየር የሚረዱ ማዕቀፎችን ሊሰጡ እንደሚችሉ ከገለጹ በኋላ፥ እነዚህ ሁለት ቡድኖች ሲተባበሩ፣ “ተፅእኖው ጥልቅ ይሆናል” በማለት ገልጸዋል።

የኖርዌይ ቤተክርስቲያን አባል እና የአውሮፓ የሃይማኖት መሪዎች ምክር ቤት ፕሬዝደንት የሆኑት ብጹእ አቡነ ካሪ ማንግሩድ በበኩላቸው ለተሰብሳቢዎች ባደረጉት ንግግር፥ መረጃዎች እንደሚያሳዩት የኖርዌይ ህዝብ ቤተክርስቲያኒቱ በሀገሪቱ ውስጥ የምታከናውነው የጋብቻ፣ የጥምቀት እና የሠርግ እንቅስቃሴ በተጨማሪ ይበልጥ የሚያደንቁት በችግር ጊዜ በሁሉም ቦታ መገኘቷን እንደሆነ ያሳያል ብለዋል።

ይህ በተለይ ዛሬ ባለው ማህበረሰብ ውስጥ ለሃይማኖቶች ጠቃሚ ሚና እንዳለው ጠቁመው፥ ማህበረሰብን በመገንባት እና በመደገፍ የሃይማኖት ተቋማት የእኛን “የብቸኝነት ወረርሽኝ” መዋጋት ይችላሉ በማለት ገልጸዋል።

የዓለም አቀፍ የውይይት ማዕከል ውይይትን በማበረታታት ረገድ ያለው “ልዩ” ሚና
አምባሳደር አልሜዳ ሪቤሮ የመግቢያ ንግግራቸውን ካደረጉ በኋላ ከቫቲካን ዜና ጋር ባደረጉት ቆይታ ጉባኤውን በማዘጋጀት ረገድ ቁልፍ ሚና የተጫወተውን የዓለም አቀፍ የውይይት ማዕከል ታሪክ እና ሚና በማንሳት ተወያይተዋል።

የዓለም አቀፍ የውይይት ማዕከል እ.አ.አ. በ 2012 ዓ.ም. በስፔን፣ ፖርቱጋል፣ ሳዑዲ አረቢያ እና በቅድስት መንበር መካከል ያለውን አጋርነት ለማጠናከር በሚል መመስረቱን የገለጹት አምባሳደሩ፥ የድርጅቱ የቦርድ አባላት ከክርስቲያን፣ ሙስሊም፣ አይሁድ፣ ሂንዱ እና የቡዲስት ሃይማኖት የተውጣጡ መሆናቸውን አብራርተዋል።

ከዚህም በተጨማሪ አምባሳደር አልሜዳ-ሪቤሮ እንዳብራሩት ድርጅቱ ከዓለም አቀፍ ተቋማት፥ ለአብነትም ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት፣ ከአረብ ሊግ፣ ከአፍሪካ ህብረት እና ከዓለም አቀፍ የስደተኞች ድርጅት ጋር በአጋርነት እንደሚሰራ ገልጸዋል።

ይህ “ልዩ መዋቅር”፣ ድርጅቱ በሃይማኖቶች እና ባህሎች መካከል ውይይቶችን በብቃት እንዲያበረታታ ያስችለዋል ያሉት አምባሳደሩ፥ በተለይ ጦርነት፣ ጅምላ ፍልሰት እና ማህበራዊ ውጥረት ባለበት ወቅት በጣም ጠቃሚ ተግባር ነው ብለዋል።

አምባሳደር አልሜዳ-ሪቤሮ በመጨረሻም የዓለም አቀፍ የውይይት ማዕከል ዓላማ፣ “ሁሉም ሰው የሚኖርባት የጋራ ምድራችንን ለመገንባት በሰዎች፣ በማህበረሰቦች፣ በባህሎች እና በሃይማኖቶች መካከል የመገናኛ ድልድይ በመሆን ለመርዳት ነው” በማለት አጠቃለዋል።
 

10 Apr 2025, 11:02