ፈልግ

ሄይቲያዊያን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣውን ብጥብጥ ለመቃወም አደባባይ ወጥተዋል ሄይቲያዊያን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣውን ብጥብጥ ለመቃወም አደባባይ ወጥተዋል   (ANSA)

በሄይቲ በወሮበሎች በተፈጸመ ጥቃት ሁለት መነኮሳት መገደላቸው ተነገረ

የሽግግር ምክር ቤቱ ከተማዋን መልሶ ለመቆጣጠር ባደረገው ሙከራ የጎዳና ላይ ወሮበሎች ጥምረት በሚሬባሌስ ከተማ ባደረሱት ጥቃት ከተገደሉት 5 ሰዎች መካከል ሁለት የካቶሊክ ቤተክርስቲያን መነኮሳት ይገኙበታል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

የቅድስት ቴሬሳ ማህበር አባል የሆኑ ኢቫኔት ኦኔዛየር እና ጄን ቮልቴር የተባሉ ሁለት መነኮሳት በሄይቲ ማዕከላዊ ዲፓርትመንት ክልል ተገድለዋል። መነኮሳቱ የተገደሉት በሀገሪቱ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ጠንካራ የወሮበላ ቡድኖችን አንድ ላይ ያሰባሰበው ‘ቪቭሬ ኤንሴምብል’ የተሰኘው ጥምረት የሽግግር ምክር ቤቱ ብሔራዊ ደህንነቱን ወደ ነበረበት ለመመለስ ላደረገው ጥረት ምላሽ ለመስጠት በወሰዱት ኃይለኛ ጥቃት እንደሆነ ተነግሯል።

ብጥብጥ ውስጥ ያለ ህዝብ
የሽግግር ምክር ቤቱ ፕሬዝዳንት ፍሪትዝ አልፎንሴ ጂን ለሃገሪቱ ሚዲያ በሰጡት መግለጫ “ጦርነት ላይ ነን” ማለታቸውን የተዘገበ ሲሆን፥ ፕረዚዳንቱ በመግለጫው ላይ የተናገሯቸው ንግግሮች የካረቢያኗ አገር ሄይቲ ላይ እየደረሰ ያለው ቀውስ አሳሳቢ መሆኑን ያሳያል ተብሏል።

ሰኞ ዕለት የቪቭሬ የወሮበሎች ቡድን ስብስብ ከፖርት-አው-ፕሪንስ በ60 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ሚሬባሌስ ከተማ ላይ ጥቃት የሰነዘረ ሲሆን፥ የሃገሪቱ የጸጥታ ሃይሎች ጣልቃ ቢገቡም ወንበዴዎቹ ከተማዋን እየተቆጣጠሩ እንደሚገኙ እየተነገረ ይገኛል።

በፍርሃት ውስጥ ያለ ማህበረሰብ
በሃገሪቷ እየተከሰተ ያለው ብጥብጥ ተባብሶ በመቀጠሉ ነዋሪዎቹ በአቅራቢያው በሚገኙ መንደሮች መሸሸጊያ ፍለጋ እንዲሰደዱ ያደረጋቸው ሲሆን፥ እስካሁን ድረስ ሁለቱን ገዳማዊያት እህቶች ጨምሮ ቢያንስ አምስት ሰዎች በጥቃቱ ህይወታቸውን አጥተዋል።

የፖርት ኦ-ፕሪንስ ሊቀ ጳጳስ ብጹእ አቡነ ማክስ ሌሮይ ሜሲዶር የሟቾቹን ማንነት ያረጋገጡ ሲሆን፥ ብጹእነታቸው እንደተናገሩት የአሁኑ ግድያ በ 2014 ዓ.ም. የተገደሉትን የእህት ሉዊዛ ዴል ኦርቶ እና እንደገና በዛው ዓመት ጥር ወር ላይ ታግተው ከሳምንታት በኋላ የተለቀቁትን ስድስት ገዳማዊያት እህቶች ያስታውሰናል ብለዋል።

ሚሬባሌስ ላይ የተፈጸመው ጥቃት
200,000 ህዝብ የሚኖርባት ሚሬባሌስ ተደጋጋሚ የወሮበሎች ጥቃት የሚደርስባት ሲሆን፥ በቅርቡ የተካሄደው ጥቃት የሽግግር ምክር ቤቱ በወንጀለኛ ቡድኖች ላይ የወሰደውን እርምጃ ለመበቀል የተወሰደ እርምጃ እንደሆነ ይነገራል።

እንደከዚህ ቀደሞቹ ድርጊቶች የወሮበሎቹ ቡድን አባላት በአካባቢው በሚገኘው እስር ቤት ውስጥ ዘልቀው በመግባት በትንሹ 500 የሚሆኑ እስረኞችን ያስፈቱ ሲሆን፥ እንደ ሄይቲ ታይምስ ዘገባ፣ ከሃገሪቱ ብሔራዊ ፖሊስ አባላት ጋር በተደረገ የተኩስ ልውውጥ ወደ 30 የሚጠጉ የወሮበሎች ቡድን አባላት መገደላቸው ተነግሯል።

ከተማዋ ውስጥ በየቀኑ በሺዎች ለሚቆጠሩ ሰዎች የጤና አገልግሎት የሚሰጠው እና ሃገሪቱ ውስጥ ከሚገኙት እጅግ የላቀ የሕክምና ተቋም የሆነው የዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል ስለሚገኝ የሚሬባሌስ ከተማን ወሳኝ ቦታ ያደርጋታል ተብሏል። ከዚህም በተጨማሪ ዋና ከተማዋን ከሰሜናዊ የባህር ዳርቻ እና ከዶሚኒካን ሪፐብሊክ ጋር የሚያገናኘው ዋና መንገድ የሚያልፍባት በመሆኑ እየተካሄደ ባለው ግጭት ውስጥ ከተማዋን ቁልፍ ኢላማ አድርጓታል።

የተባበሩት መንግስታት ተግባራዊ እርምጃ እንዲወሰድ ጥሪ ማቅረቡ
በሃገሪቷ እየተካሄደ ያለው ብጥብጥ ዓለም አቀፍ ስጋትን የፈጠረ ሲሆን፥ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሃፊ የሃገሪቱ ባለስልጣናት ከዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ድጋፍ ጋር በመሆን ጸጥታውን ወደነበረበት ለመመለስ፣ ሰላማዊ ዜጎችን ለመጠበቅ እና ወደ ዴሞክራሲያዊ አስተዳደር ለመመለስ የሚያስችሉ ሁኔታዎችን ለመፍጠር ጥረቶችን እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርቧል። ሆኖም የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብት ባለስልጣን ዊልያም ኦኔል በበኩላቸው በአከባቢው ያለውን አሳዛኝ ሁኔታን ሲገልጹ፥ “በአሁኑ ጊዜ ወደ ዋና ከተማው ከሄሊኮፕተር በስተቀር ደህንነቱ የተጠበቀ የመግቢያ ወይም የመውጫ መንገዶች የሉም” ያሉ ሲሆን፥ ወሮበሎቹ ሁሉንም ሰፈሮች በመቆጣጠር በመኖሪያ ቤቶች፣ በትምህርት ቤቶች እና በአብያተ ክርስቲያናት ላይ ግድያ፣ አስገድዶ መድፈር እና የእሳት ቃጠሎ ማድረሳቸውን ገልጸዋል።

በዋና ከተማው ላይ የተደረጉ ተቃውሞዎች
የጸጥታ ሁኔታው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ በመምጣቱ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ረቡዕ ዕለት በፖርት ኦ-ፕሪንስ ጎዳናዎች ላይ በመውጣት በአሌክስ ዲዲየር ፊልስ አይሜ የሚመራው የመንግስት ጥምረት የሀገሪቱን ደህንነት ማስጠበቅ አልቻለም በሚል ክስ ከስልጣናቸው እንዲለቁ ጥያቄ አቅርበዋል። 

በተቃዋሚዎች እና በፖሊስ መካከል የተፈጠረው ግጭት በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት እና በሽግግር ምክር ቤት ዋና መሥሪያ ቤት ላይ የመሳሪያ ጥቃቶችን ጨምሮ ተጨማሪ ብጥብጥን አስከትሏል።

እንደ የተባበሩት መንግስታት መረጃ ከሆነ ከሃምሌ 2016 እስከ የካቲት 2017 ዓ.ም. ድረስ በሄይቲ ከ4,200 በላይ ሰዎች የተገደሉ ሲሆን፥ ሌሎች 6,000 ሰዎች ደግሞ ቤታቸውን ጥለው ለመሰደድ ተገደዋል። ቀውሱ ከጊዜ ወደ ጊዜ ተባብሶ በመቀጠሉ የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በአስቸኳይ ጣልቃ እንዲገባ ጥሪ እየተደረገ ይገኛል።
 

04 Apr 2025, 13:06