ፈልግ

የእስራኤል ጦር የመልቀቂያ ትእዛዝ ካወጣ በኋላ ፍልስጤማውያን ሰሜናዊ ጋዛን ለቀው ወጥተዋል የእስራኤል ጦር የመልቀቂያ ትእዛዝ ካወጣ በኋላ ፍልስጤማውያን ሰሜናዊ ጋዛን ለቀው ወጥተዋል   (ANSA)

እስራኤል ጋዛ ላይ ባደረሰችው ጥቃት ጉዳት ከደረሰባቸው ውስጥ ጋዜጠኞች እንደሚገኙበት ተነገረ

እስራኤል ሰኞ ማለዳ ጋዛ በሚገኙት ሁለት ዋና ዋና ሆስፒታሎች አቅራቢያ የነበሩ ድንኳኖች ላይ ባደረሰችው ጥቃት ቢያንስ ሁለት ሰዎች ሲሞቱ ዘጠኝ ቆስለዋል ሲሉ የፍልስጤም የጤና ባለስልጣናት አስታውቀዋል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

እስራኤል መጋቢት 29 ቀን 2017 ዓ.ም. ጋዛ ውስጥ በሚገኙ ሁለት ዋና ዋና ሆስፒታሎች አከባቢ በነበሩ የጋዜጠኞች ድንኳን ላይ ባደረሰችው የአየር ላይ ጥቃት ከባድ ጉዳት በማድረስ ቢያንስ ሁለት ሰዎች ሲሞቱ ዘጠኝ ሰዎች ደግሞ መቁሰላቸውን የፍልስጤም የጤና ባለስልጣናት አስታውቀዋል።

ከሟቾቹ መካከል ለ ‘ፓላስታይን ቱዴይ ቲቪ’ ይሰራ የነበረው ጋዜጠኛ ዩሱፍ አል-ፋቃዊ አንዱ ሲሆን፥ ከቆሰሉት መካከል ደግሞ 6 ጋዜጠኞች እንደሚገኙበት የጤና ጥበቃ ባለስልጣናት ተናግረዋል።

በናስር ሆስፒታል አቅራቢያ የሚገኘው የተለያዩ የሚዲያ ባለሙያዎች ይገኙበት የነበረው ድንኳን ከጠዋቱ 2 ሰዓት ላይ ጥቃት ከደረሰበት በኋላ በእሳት መያያዙን የፍልስጤም ባለስልጣናት ሪፖርት አድርገዋል።

የእስራኤል መከላከያ ሚንስቴር ጥቃቱ በሃማስ ተዋጊ ሃይሎች ላይ ያነጣጠረ እንደሆነ ቢገልጽም ስለ ጥቃቱ ምንም ተጨማሪ መረጃ አልሰጠም።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የፍልስጤም ቀይ ጨረቃ ባለፈው ሳምንት በጋዛ በደረሰው የ15 የአምቡላንስ እና የእርዳታ ሰራተኞችን ሞት በተመለከተ ዓለም አቀፍ ምርመራ እንዲደረግ ጠይቋል። ሰራተኞቹ መጋቢት 14 ቀን 2017 ዓ.ም. በእስራኤል ወታደሮች በጥይት ተመተው መገደላቸው ይታወሳል።

የፍልስጤም ቀይ ጨረቃ፣ የጋዛ ሲቪል መከላከያ ኤጄንሲ እና ከመንግሥታቱ ድርጅት የፍልስጤም ስደተኛ ተልዕኮ የተውጣጡ የአስቸኳይ ጊዜ ምላሽ ቡድን የቆሰሉ ሰዎችን ለማከም ወደ ራፋ ከተማ እያቀኑ ነበር በእስራኤል ወታደሮች ጥቃት የደረሰባቸው።

የእስራኤል መከላከያ ተሽከርካሪዎቹ መብራቶቻቸውን አጥፍተው ወደ ወታደሮቹ ሲጠጉ አጠራጣሪ ሆነው በመታየታቸው እርምጃ ለመውሰድ እንደተገደደ ቢገልጽም አንዳንድ የወጡ የተንቀሳቃሽ ምስል ማስረጃዎች ግን ይሄንን እንደማያረጋግጡ ተገልጿል።

የእስራኤል ጦር በክስተቱ ዘጠኝ የሀማስ እና የፍልስጤም አክራሪ ቡድን አባላት መገደላቸውንም አስታውቆ የነበረ ቢሆንም፥ እሁድ ዕለት እስራኤል የተሳሳተ መረጃ እንደደረሳት እና ጉዳዩን በማጣራት ላይ እንደሆነ የገለጸች ሲሆን፥ የቀይ ጨረቃ በበኩሉ የአምቡላንስ ሠራተኞቹ ጥቃት የደረሰባቸው ሆን ተብሎ “ለመግደል በማሰብ ነው” በማለት ገለልተኛ ዓለም አቀፍ ምርመራ እንዲደረግ ጠይቋል።

ከዚህ ጥቃት ብቸኛ የተረፈው ሙንተር የተባለ የህክምና ባለሙያ ጉዳዩን አስመልክቶ እንደተናገረው፥ “ሌት ከቀን ተመሳሳይ ነገር ነው፥ የውጭ እና የውስጥ መብራት በርቷል፥ ሁሉም ነገር ተሽከርካሪው የፍልስጤም ቀይ ጨረቃ ንብረት የሆነ አምቡላንስ እንደሆነ ይናገራል። ሁሉም መብራት ቀጥታ እስኪተኮስብን ድረስ እየበራ ነበር” በማለት ገልጿል።

በሌላ ዜና እሁድ ዕለት በደቡባዊ እስራኤል ላይ በተፈፀመ የሮኬት ጥቃት ሶስት ሰዎች ቀላል ጉዳት የደረሰባቸው ሲሆን፥ የእስራኤል እና የፍልስጤም ምንጮች እንደገለፁት የእስራኤል ጦር በማዕከላዊ ጋዛ ላይ በርካታ የአየር ድብደባዎችን በማድረግ ምላሽ ሰጥቷል።

ባለፈው እሁድ፣ የሐማስ ወታደራዊ ክንፍ የሆነው የአልቃሳም ብርጌድ፣ በደቡባዊ እስራኤል በምትገኘው አሽዶድ ከተማ ላይ በርካታ ሮኬቶችን መተኮሱን የገለጸ ሲሆን፥ ጥቃቱ እስራኤል የፍልስጤም ሲቪሎች ላይ ለምትፈጽመው “ጭፍጨፋ” የበቀል እርምጃ ነው በማለት ገልጿል።

እስራኤል ከመጋቢት 9 ጀምሮ በጋዛ ላይ መጠነ ሰፊ የአየር እና የምድር ጥቃቶችን መፈጸሟን የቀጠለች ሲሆን፥ ይህም በመካሄድ ላይ ባለው ግጭት ውስጥ ጉልህ የሆነ መባባስ ማስከተሉ እየተገለጸ ይገኛል።

የጋዛ ጤና ባለስልጣናት እንደገለፁት እነዚህ እንደአዲስ ተጠናክረው በቀጠሉት ጥቃቶች እስከ እሁድ ድረስ ብቻ 1,335 ፍልስጤማውያን መሞታቸው እና 3,297 ደግሞ መቁሰላቸውን ይፋ አድርገዋል።
 

08 Apr 2025, 15:37